ኮሪያ ሪፐብሊክ የጫማ ምርት ዘርፍ ማሳደግ አላማ ላደረገው ፕሮጀክት የ10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ልታደርግ ነው 

101


አዲስ አበባ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ):-ኮሪያ ሪፐብሊክ በኢትዮጵያ የጫማ ምርት ዘርፍን ማሳደግ አላማ ላደረገው ፕሮጀክት የ10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች።
ፕሮጀክቱ በቡሳን ሜትሮፖሊታን ከተማ ይፋ ሆኗል።


‘ቡሳን ኢኮኖሚክ ፕሮሞሽን ኤጀንሲ’ በተሰኘው የጫማ ኢንዱስትሪ ማስተዋወቂያ ማዕከል አማካኝነት የሚተገበረው ፕሮጀክት በጫማ ምርት ዘርፍ የኢትዮጵያን አቅም መገንባት ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።


 


ፕሮጀክቱ ከእ.አ.አ 2023 እስከ 2027 የሚተገበር ሲሆን ለጫማ አምራቾች ድጋፍና ስልጠና በመስጠት በኢትዮጵያ የቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ በተለይም የጫማ ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን የመጨመር ግብ እንዳለው ገልጿል።


የኮሪያ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ(ኮይካ) ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገውን የ10 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚሸፍንም ተመላክቷል።


በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ሁለቱ አገራት ያላቸውን ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ወዳጅነት አንስተዋል።


የአገራቱ ግንኙነት በፖለቲካ እና ኢኮኖሚው መስክ ይበልጥ የመጠናከር አቅም እንዳለው ገልጸው ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ያሉ የጫማ አምራቾች ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።


ኢትዮጵያ ካላት ወጣት የሰው ኃይል እና እምቅ ሀብት አኳያ በቆዳ እና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ የውጭ ኢንቨስትመንትን የተሻለ የመሳብ አቅም ባለቤት መሆኗን ተናግረዋል።


አምባሳደር ደሴ ለ‘ቡሳን ኢኮኖሚክ ፕሮሞሽን ኤጀንሲ’ እና ቡሳን ሜትሮፖሊታን ከተማን ለፕሮጀክቱ እውን መሆን ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


 


ከአቅም ግንባታ ፕሮጀክቱ ይፋ ማድረጊያ መርሐ-ግብር ጎን ለጎን በኮሪያ ሪፐብሊክ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ‘ቡሳን ኢኮኖሚክ ፕሮሞሽን ኤጀንሲ’ በተሰኘው የጫማ ኢንዱስትሪ ማስተዋወቂያ ማዕከል የሁለቱን አገራት ትብብር ማጠናከር የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።


በተጨማሪም አምባሳደር ደሴ ዳልኬ በቡሳን ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የጫማ ፋብሪካዎች እንዲሁም የጫማ ኢንዱስትሪ ማስተዋወቂያ ማዕከል ሰርቶ ማሳያ እና ስልጠና ማዕከል ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም