የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከውጭ እና ከውስጥ የተደቀኑ አደጋዎች መመከት አስችሏል-ዶክተር አለሙ ስሜ - ኢዜአ አማርኛ
የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከውጭ እና ከውስጥ የተደቀኑ አደጋዎች መመከት አስችሏል-ዶክተር አለሙ ስሜ
አዲስ አበባ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከውጭ እና ከውስጥ የተደቀኑ አደጋዎችን መመከት ማስቻሉን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ።
"የሎጂስቲክስ ብቃት እና የተቋማት ቅንጅት ለዘላቂ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን" በሚል መሪ ቃል የግንዛቤ ማስጨበጫና የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር አለሙ ስሜ ፤ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ለውጦችን እያስመዘገበች መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው ብለዋል።
በተለይም አለም በእጅጉ እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት እየተተገበረ ያለው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከውጭም ከውስጥም የተደቀኑ አደጋዎችን ለመመከት ማስቻሉን ገልጸዋል።
የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ አካል ሆኖ እንዲተገበር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጸደቁት መካከልም የሎጂስቲክስ ዘርፍ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የወጪ ገቢ ንግድ እንዲሁም የአገር ውስጥ ምርት ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተናግረዋል።
ይህን እየጨመረ ያለውን የገቢና ወጭ ንግድ መጠን ለማስተናገድ የሚያስችሉ በርካታ የልማት ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
እንቅስቃሴው ከአገሪቱ የገቢና ወጭ ንግድ እድገት አንጻር ሲታይ በብዙ ፈተናዎች የታጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከሶስት አመት በፊት የሎጅስቲክስ ስትራቴጂ መቀረጹን አስታውሰው ይህንን ማእከል በማድረግና በየጊዜው በማሻሻል በተሻለ ቁመና ላይ ሆኖ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በሎጂስቲክስ ዙሪያ እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ዘርፉ የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የክልል ምክትል ርእሳነ መስተዳደሮች የትራንስፖርት እና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊዎች ታድመዋል።