የዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ ተጠባቂውን ጨዋታ ዛሬ ያደርጋሉ

380

አዲስ አበባ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ-ግብር የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ተከታዩ ባህር ዳር ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ በእግር ኳስ አፍቃሪው በኩል በጉጉት ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል።

ጨዋታው በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ግንቦት 18/2015 መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በከባድ ዝናብ ምክንያት ሜዳው ማጫወት ባለመቻሉ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሞ የቆየ ነው።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የውድድር እና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ጨዋታው በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስታዲየም እንዲደረግ መወሰኑ ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት የሁለቱ ክለቦች ወሳኝ ጨዋታ ዛሬ ይከናወናል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ58 ነጥብ 1ኛ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ በ53 ነጥብ 2ኛ ደረጃን ይዟል።

በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚሰለጥነው ቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ አሁን በፕሪሚየር ሊጉ ካደረጋቸው 26 ጨዋታዎች 17ቱን ሲያሸንፍ 2 ጊዜ ተሸንፎ፤ 7 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

በ26ቱ ጨዋታዎች ፈረሰኞቹ 48 ግብ ሲያስቆጥሩ 17 ጎሎችን አስተናግደዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች በሶስቱ አሸንፎ በአንድ ተሸንፎ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።


 

በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 26 ጨዋታዎች 15ቱን ሲያሸንፍ በሶስቱ ተሸንፎ፤ በ8ቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

የጣና ሞገዶቹ በ26ቱ ጨዋታዎች 47 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ 24 ግቦችን አስተናግደዋል።

ባህር ዳር ከተማ ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ሶስቱን አሸንፎ አንዱን ተሸንፎ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከተከታዩ ባህር ዳር ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስምንት ከፍ በማድረግ 16ኛውን የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ ለማንሳት ይበልጥ ይቃረባል።

በአንጻሩ ባህር ዳር ከተማ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ የሚጠበቅበት ሲሆን ጨዋታውን ካሸነፈ ከፈረሰኞቹ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ያደርጋል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር በ10ኛ ሳምንት በድሬዳዋ ስታዲየም ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

በተስተካካይ ጨዋታው ምክንያት በ28ኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና ሊያደርጓቸው የነበሩ ጨዋታዎች ሰኔ 18 2015 እንደሚከናወኑ የፕሪሚየር ሊግ የውድድር እና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም