ቁመተ መለሎው አትሌት የተናገረውን በተግባር ፈጽሟል

398

“የዓለም ክብረ ወሰን መስበሬ አላስገረምኝም ምክንያቱም ክብረ ወሰኑን እንደማሻሽለው አውቅ ነበር” አትሌት ለሜቻ ግርማ 
ወጣቱ አትሌት 19 ዓመት ያልተደፈረውን ክብረ ወሰን ሰባብሮታል። ማይክሮ ሰኮንድ
አዲስ አበባ ሰኔ 3/2015(ኢዜአ):- የዓለም አትሌቲክስ ትናንት በፓሪስ ሰባስቲያን ቻርሌቲ ስታዲየም የተደረገውን የዳይመንት ሊግ ውድድር “አስደናቂ እና የእብደት ምሽት” ሲል ገልጾታል።
በውድድሩ ሶስት የዓለም ክብረ ወሰኖች ተሰባብረዋል።
በዓለም አትሌቲክስ የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ውድድሮች ስማቸው ቀድሞ ከሚነሱ ተወዳዳሪዎች ይገኝበታል።


 

ከልጅነቱ ጀምሮ ባለው ቁመት እና ቁመና ጥሪ እና መክሊቱ አትሌቲክስ ነው ያሉ ብዙዎች ናቸው።
3 ሺህ ሜትር መሰናክልን በተደጋጋሚ ጊዜ ከስምንት ደቂቃ በታች በመግባት የሚስተካከለው የለም።
በኦሊምፒክ እና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርቀቱ የብር ሜዳሊያዎችን አግኝቷል።
ባለ ረጅም ቅልጥሙ አትሌት በውድድር ያለውን የእግር አጣጣል እና የአጨራረስ ብቃት ከብዙ የአትሌቲክስ ተንታኞች ውዳሴን አምጥቶለታል።
የዓለም አትሌቲክስ “እያበበ ያለው ወጣቱ ኮከብ” ሲል ይገልጸዋል።
በዓለም አትሌቲክስ የዓለም ምርጥ ወጣት አትሌት ሽልማት እጩዎች ውስጥ ገብቶ ያውቃል። የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን የአፍሪካ ወጣት ምርት አትሌት ሽልማት አሸናፊም ነው።
የኬንያውያን የ”ባህል ስፖርት” ነው በሚባለው የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል የኬንያ አትሌቶችን በማሸነፍ ውድድሩ የአንድ አገር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም መሆኑን አስመስክሯል።
የዓለም የ3 ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ክብረ ወሰን ባለቤት ነው።
እያወራን ያለነው ከአሰላ ስለ ተገኘው እና 1 ሜትር ከ 85 ስለሚረዝመው የ22 ዓመቱ ቁመተ መለሎ አትሌት ለሜቻ ግርማ ነው።
ትናንት በፓሪስ የዘንድሮው ዓመት የአራተኛ ዙር የዳይመንድ  ሊግ ውድድር ተካሄዷል።


 

በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ውድድር አትሌት ለሜቻ ግርማ 7 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ከ11 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት ለ19 ዓመታት በኳታሪው አትሌት ሳይፍ ሰኢድ ሻሂን ተይዞ የነበረውን የርቀቱን ክብረ ወሰን በ1 ሴኮንድ ከ52 ማይክሮ ሴኮንድ አሻሽሎታል።
አትሌት ለሜቻ በመጨረሻው ዙር ብቻውን ተነጥሎ በመውጣት እና ፍጥነቱን በመጨመር ያሳየው አጨራረስ አስደናቂ የሚባል ነበር።
አትሌቱ ከውድድሩ በፊት የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ክብረ ወሰንን ለመስበር እንደሚሮጥ ገልጾ ነበር።
አትሌት ለሜቻ የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ክብረ ወሰን የመስበር የሁልጊዜ ሕልሙን አሳክቷል ።
“በማሸነፌ በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲል አትሌት ለሜቻ ከውድድሩ በኋላ ለዓለም አትሌቲክስ በሰጠው አስተያየት ገልጿል። 
“ዓመቱን የጀመርኩት የ3 ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ ክብረ ወሰን በመስበር ነው፤ በጣም ደስ ብሎኛል ኮርቻለሁ ደስ ብሎኛል” ብሏል።
“በውድድሩ በጣም በፍጥነት ስሮጥ እንደነበር ተሰምቶኛል በራስ መተማመን ላይ ነበርኩኝ፤ የዓለም ክብረ ወሰኑ አላስገረመኝም በፓሪስ እንደማሻሽለው አቅጄ ነበር ድሉ የሙሉ ቆራጥነት ውጤት ነው” ያለው አትሌት ለሜቻ።
እንደተለመደው የአትሌቴ ክብረ ወሰን በዓለም አትሌቲክስ ክብረ ወሰንን አጣርቶ የማጽደቅ ሂደት ውስጥ ያልፋል።
አትሌቱ  የክብረ ወሰኑ ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጠው የዓለም አትሌተክስ የገባበትን ሰአት አጣርቶ ሲያጸድቅ ነው።
በውድድሩ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አብርሃም ስሜ አራተኛ ወጥቷል።


 

ትናንት በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች በተደረገው ውድድር ኬንያዊቷ አትሌት ፌይዝ ኪፕዬጎን 14 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ20 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ላለፈው ሶስት ዓመት ተይዞ የነበረውን የርቀቱን የዓለም ክብረ ወሰን በ 1 ሴኮንድ ከ42 አሻሽላለች።
በውድድሩ ኬንያዊቷ አትሌት ከኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ጋር እልህ አስጨራሽ ፉክክር አድርጋለች።
አትሌት ለተሰንበት 14 ደቂቃ ከ 7 ሴኮንድ ከ94 ሴኮንድ በመግባት ሁለተኛ ወጥታለች።
ሌላኛዋ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሯን አጠናቃለች።
ኬንያዊቷ አትሌት ፌይዝ ኪፕዬጎን ባለፈው ሳምንት በጣልያን ፍሎረንስ ከተማ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች ውድድር 3 ደቂቃ ከ49 ሴኮንድ ከ11 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት በአትሌት ገንዘቤ ዲባባ ተይዞ የነበረውን የርቀቱን የዓለም ክብረ ወሰን በአንድ ሴኮንድ ማሻሻሏ የሚታወስ ነው።
አትሌቷ በስምንት ቀናት ውስጥ ሁለት የዓለም ክብረ ወሰን በመስበር አዲስ ታሪክ ጽፋለች።

በ2 ማይል የወንዶች ውድድር የ22 ዓመቱ ኖርዌያዊ አትሌት ጃኮብ ኢንግብሪግስተን 7 ደቂቃ ከ54 ሴኮንድ ከ10 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት የርቀቱን የዓለም ክብረ ወሰን ሰብሯል።
በፓሪስ የተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሶስት የዓለም ክብረ ወሰኖች የተሰበሩበት ታሪካዊ ምሽት ሆኖ አልፏል።
የዘንድሮው አምስተኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሰኔ 8 2015 በኖርዌይ ኦስሎ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም