የሀገር አቀፍ ሕግ አውጪዎች የጋራ የምክክር መድረክ በጅግጅጋ ይካሄዳል

ጅግጅጋ ሰኔ 2/2015(ኢዜአ)፦ የሀገር አቀፍ ሕግ አውጪዎች የጋራ የምክክር መድረክ ነገ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እንደሚካሄድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉበዔ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ፣በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ፣ የፍትሕ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የፌዴራል፣ የክልል እና የሁለቱ ከተማ መስተዳደር ምክር ቤቶች አፈ-ጉባዔዎች ማምሻውን ጅግጅጋ ከተማ ገብተዋል።

የሕግ አውጪዎቹ ጅግጅጋ ሲደርሱ በሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ ዑመር እና በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ነገ የሚካሄደው መድረክ በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት፣ እንዲሁም በክልሎች መንግስታት መካከል ያለው ግንኙነት ጥንካሬዎች ለማስቀጠል እና የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን ለመሙላት ያለመ ነው።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ ዋስትና ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማረጋገጥ፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማትን ለማስቀጠል የመድረኩ ፋይዳ የጎላ እንደሚሆን በሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት የሚዲያ ዘርፍ ዳይሬክተር ወይዘሮ ብስራት ሽፈራው ገልጸዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም