ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያላትን የኢኮኖሚ ድርሻ ለማሳደግ እየተሰራ ነው - የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያላትን የኢኮኖሚ ድርሻ ለማሳደግ እየተሰራ ነው - የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሰኔ 2/2015(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ ከምርትና አገልግሎት ጥራት ጋር ተያይዞ የሚገጥማትን ችግሮች በመፍታት በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያላትን የኢኮኖሚ ድርሻ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
ዓለም አቀፍ አክሪዲቴሽን ቀን “አክሪዲቴሽን ቀጣይ የዓለም አቀፍ ንግድን ያግዛል” በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ዛሬ አክብሯል።
በሕክምናና በፍተሻ ላቦራቶሪዎችና በኢንስፔክሽን ለሚሰሩ ሰባት ተቋማት የአክሪዲቴሽን ሰርተፊኬት ሰጥቷል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት በሕክምና ላቦራቶሪዎችና ለሌሎች ተቋማት የአክሪዲቴሽን ዕውቅና እየሰጠ ነው።
አገልግሎቱ በዓለም አክሪዲቴሽን ፎረምና በዓለም የላቦራቶሪ አክሪዲቴሽን ትብብር ዓለም አቀፍ እውቅናን አግኝቶ በመሥራቱ የአገራችን ተስማሚነት ምዘና ተቋማት በዝቅተኛ ወጪ በአገር ውስጥ አገልግሎቱን እንዲያገኙ አስችሏል ብለዋል።
ተቋሙ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ የንግድ ቀጣና ጋር ተያይዞ መልክአ ምድር ሳይወስነው በየትኛውም ቦታ እየተገኘ የአክሪዲቴሽን አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችለው ደረጃ ላይ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
የአገር ውስጥ አምራቾችና ላኪዎች በዓለም የገበያ መዳረሻዎች የዓለምን ገበያ ሰብረው መግባት የሚችሉ ከጥራት ጋር ተያይዞ እየገጠማቸው ያለውን ፈተና ለመወጣት ብቃት ያለው የብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማት ሲኖሩ ብቻ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎትን በማጠናከር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያላትን የኢኮኖሚ ድርሻ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ባለድርሻዎችም ተቋሙ የገነባውን አቅም ተጠቅመው አገልግሎታቸው እምነት እንዲያሳድርና በተገልጋዮቻቸው ታማኝና ተወዳጅ ተቋም እንዲኖራቸው የተቋሙን አገልግሎት እንዲጠቀሙ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር መሰረት ተሰማ በበኩላቸው አክሪዲቴሽን እየተነቃቃና ዓለም ላይ ለመወዳደር አክሪዲቴሽን ግዴታ የሚሆንበት አሰራር እየመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
አገልግሎቱ ዕውቅና ባገኘባቸው የሕክምና፣ የፍተሻ፣ የኤንስፔክሽንና ላቦራቶሪና በአሰራር ሥርዓት ሰርተፊኬሽን ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዓሉ የአክሪዲቴሽን አገልግሎት ያለውን አገራዊ ጠቀሜታዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች በማመላከት ባለድርሻ አካላትና ኅብረተሰቡ ለዘርፉ ዕድገት የበኩሉን እንዲወጣ ማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ባለፉት 12 ዓመታት ለ116 ተቋማት እንዲሁም 152 አይነት የአክሪዲቴሽን አገልግሎት ሰጥቷል።