የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የኢትዮጵያን የውሃ ሀብቶችን ለመጠበቅ ጉልህ ፋይዳ ያለው ነው- የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የኢትዮጵያን የውሃ ሀብቶችን ለመጠበቅ ጉልህ ፋይዳ ያለው ነው- የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር
አርባ ምንጭ ሰኔ 2/2015 (ኢዜአ):- የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ኢትዮጵያን የውሃ ሀብቶቿን እንድትጠብቅ እና እንድታቆይ ወሳኝ አበርክቶ እንዳለው የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
21ኛው ዓለም አቀፍ የውሃ አውደ ጥናት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው፡፡
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቶቿን ጥቅም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የ10 ዓመት እቅድ ነድፋ ተግባራዊ እያደረገች ነው።
የውሃ ሀብቶችን በተቀናጀ ሁኔታ ለማስተዳደር፣ ውሃን ለመጠጥና ለኃይል አቅርቦት እንዲውል ማድረግ እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
"ውሃ ሕይወት እንደመሆኑ መጠን አስቀድመን ለውሃው ሕይወት በመስጠት ማቆየት ይገባል" ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው የውሃ ሀብቶቻችን ጥቅም ዘላቂ ለማድረግ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ መጠበቅ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የውሃ ሀብቶችን ከመጠበቅ አኳያ ትልቅ ፋይዳ አለው ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።
መርሐ-ግብሩ ለግብርና፣ኢንዱስትሪ፣ቱሪዝም፣መዝናኛ፣መጠጥ ብቻ ሳይሆን ለአገር ልማት ወሳኝ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
መንግስት ለውሃ ሀብት ልዩ ጥበቃ እና እንክብካቤ ትኩረት በመስጠት በተቀናጀ መንገድ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንትፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ቦጋለ ገብረማርያም በበኩላቸው ከውሃ ሀብት ዘርፍ ዘላቂ ጥቅም ለማግኘት የተፋሰስ አካላት እንክብካቤና ልማት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
"በዘርፉ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በኩል የተደረጉ ምርምሮች መደርደሪያ ላይ ከመቀመጥ አልፈው አስፈላጊው ጥቅም ላይ እንዲውል ትኩረት ያስፈልጋል" ብለዋል።
የካናዳ 'ኤምሲማስተር' ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፖላን ኩሊባሊ ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ ልማት የውሃ ሀብት አቅምን ከማሳደግም በላይ ለኢትዮጵያ እድገት ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት የኃይል አቅርቦት በእጅጉ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ የውሃ ሀብትን መጠበቅና በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።
21ኛው ዓለም አቀፍ የውሃ አውደ ጥናት እስከ ነገ ይቆያል።