ምሁራን ለአገራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፍላጎት የሚያሟላ እውቀትና ክህሎት እንዲፈጠር የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ተጠየቀ

312

ዲላ ሰኔ 2/2015(ኢዜአ):- ምሁራን ለአገራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ እውቀት እና ክህሎት እንዲፈጠር የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ። 

ዲላ ዩኒቨርሲቲ "ምርምር ለማህበረሰብ ለውጥ" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው  12ኛው አገር አቀፍ የምርምር አውደ ጥናት ዛሬ ተካሄዷል።

የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና መምህር ፕሮፌሰር አቢ ታደሰ ኢትዮጵያ ከፖሊሲ ማዕቀፍ ጀምሮ በሰው ሀብት ልማት እና የቴክኖሎጂ ልማት ላይ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነች ነው ብለዋል።


 

በግብርና መካናይዜሽን፣ በኢንዱስትሪ ልማት እንዲሁም ደመና የማበልጸግ ቴክኖሎጂን ጨምሮ በአየር ንብረት እና መሰል ዘርፎች ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል። 

ይሁንና ሳይንስና ቴክሎኖጂን በሙሉ አቅም ተጠቅሞ ሁለንተናዊ ለውጥ በማረጋገጡ ረገድ ገና ብዙ መስራትን እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የመጠቀም ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ ዓለም አቀፍ የእውቀትና የክህሎት ሽግግር እንዲፈጠር በትጋት መስራት ከምሁራን የሚጠበቅ ስራ መሆኑን ነው ፕሮፌሰር አቢ የገለጹት።

ከማህበራዊ ለውጥ ጋር የተቆራኘ የምርምር ስራ ከማከናወን ባለፈ ልምድና ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትስስር መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ጽዮን ሙላት በበኩላቸው በትምህርት ዘርፉ የሚገኙ ቴክኖሎጂዎች በዓለም አቀፍ ልምድ እና ተሞክሮ መዳበር እንዳለባቸው ገልጸዋል።


 

የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ የተለያዩ የሕክምና መሳሪያዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በቅንጅት መስራት ይገባል ነው ያሉት። 

የዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሃብታሙ ተመስገን በግብርናው ልማት በተለይም በደጋ ፍራፍሬ እንዲሁም በቡና ልማት የተገኙ የምርምር ውጤቶች አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረጉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህም የምርምር ስራዎች ወደ ተግባር በመቀየርና ቴክኖሎጂ በማላመዱ ረገድ እየተከናወኑ የሚገኙ ጥረቶችን የሚያጠናከር ነው ብለዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወጣጡ ምሁራን የጥናት ውጤታቸውን ያቀረቡ ሲሆን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም