የሩሲያና የኢትዮጵያ አጋርነትን በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከር እየተሰራ ነው - አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን

121


አዲስ አበባ ሰኔ 2/2015(ኢዜአ):- ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን የኢትዮጵያና የሩሲያ ወዳጅነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ለኢዜአ እንደገለጹት ሁለቱ አገራት ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው።  

የኢትዮ-ሩሲያ የመንግሥትና የሕዝብ ለሕዝብ ወዳጅነት የጋራ ጥቅምን እንዲሁም መተማመንን መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። 

እያደገ የመጣውን የሁለቱ አገራት አጋርነት በኢኮኖሚ የትብብር መስክ ይበልጥ ሊያዳብሩ የሚችሉባቸው ዕድሎች መኖሩንም ነው የገለጹት። 

ይህንንም ተከትሎ አገራቱን በምጣኔ ኃብት መስክ ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ ሰላም ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና መረጋጋት ትልቅ ትሩፉት እንዳለው ጠቁመው የኢትዮጵያ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። 

በመሆኑም በሰላም ግንባታና በሌሎች ተያያዥ ሥራዎች ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል። 

አገራቱ የሁለትዮሽ ብቻ ሳይሆን በባለብዙ ወገን መድረኮችም ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቁመው ይህንን ይበልጥ ለማጠናከር ይሰራል ነው ያሉት። 

በሌላ በኩል ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር እንደምትሰራ ገልጸዋል።

በተለይም በአፍሪካ ኅብረት ትኩረት የተሰጠው 'ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ' መርህ እውን እንዲሆን አገራቸው ጽኑ እምነት አላት ብለዋል። 

ኢትዮጵያና ሩሲያ ከ125 ዓመታት በላይ ወዳጅነት ያላቸው አገራት ናቸው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም