የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዘጠኝ የአውሮፓ ሕብረት ፕሮጀክቶችን አሸነፈ


አዲስ አበባ ሰኔ 2/2015 (ኢዜአ):- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአውሮፓ ሕብረት ከሚደግፋቸው 17 የምርምር እና የትምህርት ልህቀት ማዕከላት ፕሮጀክቶች መካከል በዘጠኙ አሸናፊ መሆኑን አስታወቀ። 

በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን እ.አ.አ ሕዳር 2022 የ ‘ARUA’ እና ‘Guild’ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች በነበራቸው ስብሰባ በአውሮፓ ሕብረት የሚደገፉ የምርምር እና የትምህርት ልህቀት ማዕከላት ለማቋቋም መወሰናቸው ይታወሳል።


 

በዚሁ መሰረት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ፕሮፖዛሎች የቀረቡ ሲሆን ባለፉት ሁለት ተከታታይ ቀናት በቤልጂየም ብራስልስ በተካሄደው ግምገማ መሰረት 17 የልህቀት ማዕከል ተመስርተዋል። 

ከነዚህ የልህቀት ማዕከል ፕሮጀክቶች ውስጥም በዘጠኙ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሸናፊ መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አመልክቷል።

በተጨማሪም የሁለት የፕሮጀክት ፕሮፖዛል ውጤት በመጪው ጥቂት ወራት እንደሚታወቅም ነው ዩኒቨርሲቲው ያስታወቀው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ይህ ውጤት ለዩኒቨርሲቲውም ሆነ ለአገር ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል።

ፕሮፌሰር ጣሰው ለተገኘው ውጤት አስተዋጽኦ ላደረጉ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች እንዲሁም በቤልጂየም ብራስልስ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም