በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል  ለአረንጓዴ አሻራ  ልማት 55 ሚሊየን   ችግኝ  መዘጋጀቱን የግብርና ቢሮ አስታወቀ

200

አሶሳ ሰኔ 2 /2015 (ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ  ልማት  የሚውል 55 ሚሊየን   ችግኝ  መዘጋጀቱን  የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ ባበክር ከሊፋ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፤ የተዘጋጀው ችግኝ ባለፈው የበጋ ወቅት የአፈርና ውሃ ጥበቃ የተካሄደበት 29 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሚተከል መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም አብዛኛው የክልሉ ህዝብ ተሳታፊ ለማድረግ መታቀዱን የገለጹት ሀላፊው፤ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የሚካሄድበት ጊዜ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የሚተከለው ችግኝ  የተፈጥሮ ሃብት መልሶ እንዲያገግም የሚያግዝ  ከመሆኑም ባሻገር  ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ቡና፣ ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ቀርከሃን ጨምሮ ሌሎች ሃገር በቀል ችግኞች እንደሚገኙበት አመልክተዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፈው ዓመት ክረምት ከተተከለው 42 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኝ  ውስጥ  ከ90 በመቶ በላይ መጽደቁን አቶ ባበክር አስታውሰዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም