ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ በኢትዮጵያ የፖርቹጋል አምባሳደር ጋር ተወያዩ 


አዲስ አበባ ሰኔ 2/2015 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ በኢትዮጵያ የፖርቹጋል አምባሳደር ሉዊሳ ፍራጎሶ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ ሁለቱ አገራት በኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ኮሚሽኑ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አመልክቷል።

ኢትዮጵያ እና ፖርቹጋል ከ14ኛ ክፍለ ዘመን አንስቶ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1984 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

አገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የካቲት 2015 በአዲስ አበባ በተካሄደው 42ኛው ከአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ ጎን ለጎን ከፖርቹጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ጆ ጎሜዝ ክራቪንሆ ጋር አገራቱ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም