ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ከኤሌክትሪክ የኃይል ሽያጭ ከ83 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች

አዲስ አበባ ሰኔ 2/2015(ኢዜአ)፦ የ2015 በጀት ዓመት 10 ወራት ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ካቀረበችው የኤሌክትሪክ የኃይል ሽያጭ ከ83 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ። 

የተቋሙ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ 10 ወራት ከመነጨው ኃይል ውስጥ 12 ሺህ 126 ጊጋ ዋት ሽያጭ መከናወኑንና የእቅዱን 85 በመቶ ማሳካት ተችሏል።

ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም በ26 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል። 

በተጠቀሰው ጊዜ ለጎረቤት አገራት ከተሸጠው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ83 ሚሊየን ዶላር በላይ መገኘቱን ተናግረዋል።

ጅቡቲ፣ኬንያ እና ሱዳን የኤሌክትሪክ የኃይል ሽያጭ የተደረገባቸው አገራት መሆናቸውን ነው አቶ ሞገስ ያመለከቱት።

በተያያዘም በበጀት ዓመቱ 10 ወራት  ከአገር ውስጥ የኃይል ሽያጭ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 20 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከጅቡቲ እና ሱዳን በተጨማሪ ከሕዳር 2015  ጀምሮ ለኬንያ የኤሌክትሪክ የኃይል መሸጥ መጀመሯ የሚታወስ ነው።

የኤሌክትሪክ የኃይል ሽያጩ ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኢኮኖሚ የማስተሳሰር እቅድ አካል እንደሆነም ይታወቃል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም