ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማሻገር የአሁኑ ትውልድ በዘመኑ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ተመለከተ

117

ሰኔ 02/2015 (ኢዜአ) ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች አገር ለማሻገር የአሁኑ ትውልድ በዘመኑ ያሉትን ፈተናዎችና መልካም አጋጣሚዎችን በበጎ ተጠቅሞ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ተመለከተ።

32ኛው የጉሚ በለል የውይይት መድረክ "ቃል እና ተግባር፡ ከትውልድ እስከ ትውልድ” በሚል መሪ ሃሳብ  በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ተካሄዷል፡፡


 

በውይይቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃይሉ አዱኛ ፤ የአንድን ትውልድ ማንነትና ምንነት የሚወስኑት ትውልዱ በዘመኑ ያሉ ፈተናዎችና መልካም አጋጣሚዎችን ለመሻገር የሚያደርጋቸው ጥረቶች ናቸው" ብለዋል።

"ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ ይገነባል" ያሉት አቶ ሃይሉ፤ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር ማሻገር የሚቻለው የአሁኑ ትውልድ በዘመኑ ያሉትን አማራጮች ተጠቅሞ ጠንክሮ ሲሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የመድረኩ መሪ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ በበኩላቸው በትልቁ የሚገነባው ማህበራዊ እሴት መነሻው ሰው ለራሱ ከሚገባው ቃል ኪዳን ነው ብለዋል።


 

ሚኒስትር ዴኤታው ትውልድም በቃሉ ላይ የተመሰረተ የሀገር ግንባታ እንደሚያካሄድ ተናግረዋል።

በመድረኩ የመነሻ የውይይት ጽሁፍ ያቀረቡት በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ  ዶክተር ዮሴፍ ቤኮ የተገባው ቃል በድርጊት የማይገለጽ ከሆነ እንደባከነ ይቆጠራል ብለዋል።

ቃል እና ተግባር እንደ ሰንሰለት የተሳሰረ ያሉ ሲሆን ትውልድም ካለፈው ከአሁኑና ከሚመጣው ጋር የተሳሰረ ነው ብለዋል።

በዚህም የመደመር ትውልድም ካለፈው የተገኘውን በጎ ውጤት እንደ ስንቅ በመያዝ ለሚመጣው ትውልድ ቃሉን ወደ ተሻለ ድርጊት መቀየር እንዳለበት በመግለጽ።

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት ተማሪዎች መካከል ከአምቦ ኢፈ ቦሩ 2ኛ ደረጃ አዳሪ ትምርት ቤት የመጣችው የ9ኛ ክፍልተማሪ ፅዮን ሁምኔሳ በሰጠችው አስተያየት፤ "እኛ የመደመር ትውልድ የቃል ብቻ ሳንሆን የተግባር ትውልድ መሆናችንንም ጠንክረን በመስራት እናስመሰክራለን ብላለች።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በመደመር ትውልድ መጽሓፋቸው አንድ ትውልድ በዘመኑ ያሉ ፈተናዎችና መልካም አጋጣሚዎችን ለመሻገር የሚያደርጋቸው ጥረቶች ከግምት በማስገባት ስለ ትውልዱ  ያሰፈሩት ሀሳብ በመድረኩ ተወስቷል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም