የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መጻሕፍት ኢትዮጵያን ለማስቀጠል መሰረት የሚጥሉ እሳቤዎችን የያዙ ናቸው - አርቲስት ደበበ እሸቱ

560

አዲስ አበባ ሰኔ 2/2015(ኢዜአ)፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሶስቱ የመደመር መጻሕፍት ኢትዮጵያን ለማስቀጠል መሰረት የሚጥሉ እሳቤዎችን የያዙ መሆናቸውን አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አዘጋጅነት "የመደመር ጉዞ" በሚል መሪ ሀሳብ በቢሾፍቱ ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል። 


 

በውይይቱም የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል። 

የመደመር እሳቤ ይዟቸው የመጡ መልካም አጋጣሚዎች፣ በሂደቱ እያጋጠሙ የሚገኙ ተግዳሮቶችና መፍትሔ አመላካች ጉዳዮችን የሚዳስሱ የማጠንጠኛ ሀሳቦች ላይ ምክክር ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመደመርን ፋይዳ የሚያመላክቱ እሳቤዎችን ያካተቱ ሶስት መጻህፍት ለንባብ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።


 

የስራ ባህልን ለማጎልበት እና በስራ ሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን መፍትሔ ለመስጠት አመላካች ሀሳቦችን መካፈል የውይይቱ ዓላማ መሆኑን አመልክተዋል።

የመደመር እሳቤ የሚቆም ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ሂደት እንደሆነም ተናግረዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ  አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ያለፈውን ዘመንና የአሁኑን ትውልድ ጉዞ እና ተሞክሮ አቅርበዋል።

ጭፍን ጥላቻ እና ትችትን በማስወገድ የተሰነዱ መጻሕፍት አንብቦ በሚገባ አሰናስሎ መገንዘብ እና መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሶስቱ የመደመር እሳቤ መጻሕፍት ቀጣይ የኢትዮጵያን እጣ ፋንታ ለመወሰን መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በውይይቱም የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የስራ ባህልን በማሻሻል ውጤታማ የልማት ምህዳርን መፍጠር እንደሚገባ ተገልጿል።

እያንዳንዱ ዜጋ በስራ ሂደት የተሻለ ትጋት እና ተነሳሽነትን በመላበስ ኢትዮጵያ ያላትን ጸጋ አልምቶ በመጠቀም እድገትና ብልጽግናዋን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም