በደብረ ኤሊያስ ወረዳ በተወሰደው ሕግ ማስከበር እርምጃ በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ሰላም ተመልሶ የግብርና ስራቸውን እያከናወኑ መሆኑን አርሶ አደሮች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በደብረ ኤሊያስ ወረዳ በተወሰደው ሕግ ማስከበር እርምጃ በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ሰላም ተመልሶ የግብርና ስራቸውን እያከናወኑ መሆኑን አርሶ አደሮች ገለጹ
ባህርዳር ሰኔ 02/2015 (ኢዜአ):- በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤሊያስ ወረዳ መንግስት በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ሰላም ተመልሶ የግብርና ስራቸውን እያከናወኑ መሆኑን የአካባቢው አርሶ አደሮች ገለጹ።
በደብረ ኤሊያስ ወረዳ በገዳም ውስጥ የመሸጉ ሽፍቶች በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ የፀጥታ ችግር በመፍጠር ሕዝቡ በሰላም እንዳይኖር አድርገውት እንደነበርም ተናግረዋል።
የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በቅርቡ በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ ሥላሴ ገዳም መሽገው መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጾ ነበር።
በወቅቱም በገዳሙ ውስጥ ለውጊያ ሲውል የነበረው ምሽግ መሰበሩንና በ200 ታጣቂዎችም ላይ እርምጃ መወሰዱን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ አስታውቆ ነበር።
ከጠቅላይ ቤተክህነት፣ ከምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት፣ ከወረዳው ቤተ ክህነት፣ ከዞንንና ከወረዳ የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች 'ብሔረ ብፁን አፄ መልክአ ስላሴ አንድነት ገዳምን ጎብኝተዋል።
በዚሁ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የደብረ ኤልያስ ወረዳ የመቤሽ ቀበሌ ነዋሪ ቄስ መሠረት ሰውነት ለኢዜአ እንደገለፁት በገዳሙ ውስጥ የመሸጉ ሽፍቶች በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ የፀጥታ ችግር ፈጥረው ነበር።
ሽፍቶቹ ነፍሰ ጡር እናቶችን ሳይቀር ''እንፈጃችኋለን'' በማለት በህብረተሰቡ ላይ ስጋት መፍጠራቸውን ጠቁመው የጸጥታ አካላት እርምጃ ከወሰዱ በኋላ የአካባቢው ሰላም መመለሱን ተናግረዋል።
''አሁን ላይ አካባቢው ሰላም በመስፈኑ ወደ እርሻ ስራችን ተመልሰን ለመጭው መኸር ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን'' ብለዋል።
በወረዳው የጓይ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሞኝሆድ ጫኔ በበኩላቸው በገዳሙ የነበሩት ሽፍቶች ሰውም ሆነ ከብት ገዳሙ አካባቢው ወደ ሚገኘው በረሃ እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ ችግር ፈጥረው ነበር ብለዋል።
''ከአባቶቻችን ጀምሮ የሚታወቀው በገዳም ውስጥ ፀሎት ይደረግበታል፣ ደካማ ይጦርበታል፣ የተጣላ ይታረቅበታል እንጅ በሽፍቶች አስነዋሪ ድርጊት ይፈጸምበታል ተብሎ ታስቦ አያውቀም'' ነው ያሉት።
ከአካባቢው ማህበረሰብ መካከል አንድ ሰው የሚፈጽሙት ድርጊት ትክክል አለመሆኑን ከተናገረ ተከታትለው በመግደል መልሰው በገዳሙ ውስጥ ይደበቁ እንደነበረም ተናግረዋል።
ጸረ ሰላም ሀይሎቹ ህዝቡን በጭንቀትና በፍርሃት ውስጥ ከተው የአካባቢው ህብረተሰብ ለከፋ ችግር ተዳርጎ ቆይቷል ብለዋል።
ሽፍቶቹ ወጣቱን ቀርቶ ነፍሰ ጡር ሴቶችን ሳይቀር ለመጨፍጨፍ ቀጠሮ ይዘው ነበረ የሚሉት አርሶ አደሩ ቢሆንም በተወሰደው እርምጃ በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ሰላም ተመልሶ የግብርና ስራቸውን በትኩረት እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር አያናው መለሰ በበኩላቸው ''ከብቶቻችንን ይዘን ወደ በረሃው ስንወርድ ከብት ጠባቂው እረኛ ሳይቀር ይደበደብ ነበር'' የአካባቢው ሰላም ወደ ነበረበት በመመለሱ ከስጋት ነፃ እንደሆኑ ተናግረዋል።
የደብረ ኤልያስ ወረዳ ዋና አሰተዳዳሪ አቶ መልካሙ አዲስ በበኩላቸው የስላሴ አንድነት ገዳም በደብረ ኤልያስ ወረዳ ህዝብ በ1992 ዓ.ም ተገንብቶ መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ገዳም መሆኑን አስታውሰዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያየ ምክንያት የሰው ነፍስ የገደሉ ግለሰቦች ሁሉ ወደ ገዳሙ ገብተው በመደበቅ ወታደራዊ ስልጠና ሳይቀር ይወስዱ እንደነበር በተለያየ ወቅት በሚደርስ ማስረጃ እንዳረጋገጡ ገልጸዋል።
ከክልሉም ብሎም ከምስራቅ ጎጃም ዞን ችግሩን ለመፍታት ሽማግሌዎችን በመላክ ጭምር ጥረት ቢያደርግም ችግሩ ሳይፈታ ቆይቷል ነው ያሉት።
በተወሰደው እርምጃም የአካባቢው ሰላም በአሁኑ ወቅት ወደ ነበረበት በመመለሱ ህብረተሰቡ ያለ ስጋት የልማት፣ የእርሻና የዘር ስራውን በአግባቡ እንዲያከናውን አስችሎታል ብለዋል።