ቀጥታ፡

የውጪ ምንዛሪን በመደበኛ አማራጭ መላክ የሚያስችል አገራዊ ንቅናቄ ሊካሔድ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 2/2015 (ኢዜአ)፡- የውጪ ምንዛሪን በመደበኛ የመላኪያ አማራጭ መላክ የሚያስችል አገራዊ ንቅናቄ ሊካሔድ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።

ንቅናቄው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለስምንተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ግዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ ''የቤተሰብ የውጪ ምንዛሪ መላኪያ ቀን''ን አስመልክቶ እንደሚካሄድ ገልጿል።

የንቅናቄ መርሐ-ግብሩ አገልግሎቱ ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት(ጂ አይ ዜድ) እንዲሁም ከሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ያዘጋጀው ነው።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንደሰን ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት የአገርን እድገት ከሚያሳልጡ ጉዳዮች መካከል የውጪ ምንዛሪ በመደበኛ የመላኪያ አማራጭ መጠቀም ይገኝበታል።

ለዚህም በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ ሰዎች ለቤተሰቦቻቸውና መሰል ጉዳዮቻቸው የሚልኩት የውጪ ምንዛሬ ተጠቃሽ መሆኑን አመልክተዋል።

በመሆኑም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ በ2015 በየዓመቱ ሰኔ ወር ''የቤተሰብ የውጪ ምንዛሪ መላኪያ ቀን'' አድርጎ የሰየመ ሲሆን አገራት እለቱን በተለያዩ መርሐ-ግብሮች ያከብራሉ።

የቀኑን አስፈላጊነት በመገንዘብ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የፊታችን ሰኔ 15 ''የቤተሰብ የውጪ ምንዛሪ መላኪያ ቀን'' በተለያዩ የንቅናቄ መርሃ-ግብሮች ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ነው አቶ ወንደሰን የገለጹት።

የንቅናቄው መርሐ-ግብር በዋናነት ለቤተሰብ የሚላክ የውጪ ምንዛሪ የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል እና የድህነት ቅነሳ ላይ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

በዕለቱ ለቤተሰብ የሚላክ የውጪ ምንዛሪ የቤተሰቦችን ሕይወት ከመቀየር ባሻገር ለአገር እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦን የሚያመላክት ጽሁፍ እንዲሁም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የውጪ ምንዛሪን ለመላክ እንደ አገር ያሉ አማራጮችና እድሎችም እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።

በዋናነት በመደበኛ አማራጮች በሚላክ የውጪ ምንዛሪ የአላላክ ሂደት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን በመለየት መፍትሔን ማበጀት ላይ ቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል ነው ያሉት።

በመርሐ-ግብሩ ላይ ለኢትዮጵያ እድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱ በተለይም በመደበኛ የመላኪያ አማራጭ የውጪ ምንዛሪን የላኩ የዳያስፖራ አባላት እውቅና እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል።

በተለያዩ የዓለም አገራት ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጪ ምንዛሪን በመደበኛ አማራጮች በመላክ እያበረከቱት ያለውን የዜግነት ኃላፊነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቶ ወንደሰን ጥሪ አቅርበዋል።

በ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በሕጋዊ መንገድ ከውጭ አገራት 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር (ሬሚታንስ) ወደ አገር ውስጥ መላኩን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 4 ቢሊዮን ዶላር ከሬሚታንስ ለማግኘት መታቀዱን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም