ቀጥታ፡

በአፋር ክልል ለህብረተሰቡ  የጤና መድህን አገልግሎትን ለማዳረስ በተጀመረው ንቅናቄ የተገኘው ውጤት አበረታች ነው- አገልግሎቱ

ሠመራ፤ ሰኔ 2 / 2015 (ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል ለህብረተሰቡ  የጤና መድህን አገልግሎት  ለማዳረስ  በተጀመረው ንቅናቄ የተገኘው ውጤት ከሌሎች አካባቢዎች የተሻለና አበረታች መሆኑን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ።

በክልሉ ቀደም ሲል በአይሳኢታና አፋምቦ ወረዳዎች የተጀመረውን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ወደ 13 ወረዳዎች ለማስፋፋት በሠመራ ከተማ  የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄዷል። 

በመረሃ ግብሩ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ  እንዳሉት፤ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በክልሉ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት የተካሄደው ንቅናቄ  አበረታች ነው። 

በክልሉ ዘንድሮ በልዩ ሁኔታ የህብረተሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አመራሩ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ በተደረገው ንቅናቄ ውጤታማ ስራ እንደተከናወነ መረዳታቸውን ተናግረዋል።

ይህም በዓመቱ በክልሉ  በተካሄደው ንቅናቄ  በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ70 ሺህ በላይ  አባላት መመዝገብ እንደተቻለ የጠቀሱት ወይዘሮ ፍሬህይወት፤ ህብረተሰቡ አገልግሎቱን በተገቢው እንዲያገኝ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

እንደ ሀገር 56 ሚሊዮን አባል አለን ብለዋል።


 

የአፋር ክልል የጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ በበኩላቸው ፤ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት በተለያየ ምክንያት ዘግይቶ በክልሉ የተጀመረው በአይሳኢታና አፋምቦ ወረዳዎች እንደነበረ አስታውሰዋል።

በአመራሩ ቁርጠኝነት  የንቅናቄ ስራ በመከናወኑ በዓመቱ በአጭር  ጊዜ  ተጨማሪ አስራ ሶስት ወረዳዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ መረሃ ግብሩ መጀመሩን ገልጸዋል።

በቀጣይም ወደ 40 ወረዳዎች ከፍ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።

በክልሉ  ስራውን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ ሞተር ብስክሌቶችና  ኮምፒውተር ከኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የተበረከተ ሲሆን፤  የክልሉ ጤና ቢሮ ካለው ተሽከርካሪ አንድ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት በአፋር ክልል አይሳኢታና አፋምቦ ወረዳዎች ሲጀመር 7ሺህ 286 አባዎራዎችና እማዎራዎችን መድረስ ሲቻል፤ ወደ 13 ወረዳዎች ሲስፋፋ ደግሞ 70ሺህ 268 አባዎራዎችና እማዎራዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም