በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እየታየ ያለው የኢንቨስትመንት ስበት መነቃቃት ተስፋ ሰጪ ነው - አምባሳደር ደዋኖ ከድር - ኢዜአ አማርኛ
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እየታየ ያለው የኢንቨስትመንት ስበት መነቃቃት ተስፋ ሰጪ ነው - አምባሳደር ደዋኖ ከድር
አዲስ አበባ ሰኔ 2/2015(ኢዜአ) ፦ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየተደረገ ያለው አነቃቂ ተግባር ተስፋ ሰጪ መሆኑን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ደዋኖ ከድር ገለጹ።
አምባሳደሩ በቻይና ይፋዊ ጉብኝት ካደረገው ከኮርፖሬሽኑ ልዑክ ጋር በኢንቨስትመንት ስበት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
አምባሳደሩ በተለይም ኮርፖሬሽኑ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በሀገር ውስጥ እንዲሁም በመላው አለም እየተንቀሳቀሰ የሚያከናውነው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን አክለዋል።
ኢንቨስትመንትን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመሳብ ተቋማት ይበልጡን ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸውና በዚህም የተጀመሩ አበረታች እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ ፤ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፤ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በጋራ ለአንድ አላማ ተቀራርበው እየሰሩ ያሉበት መንገድ አበረታች መሆኑን አንስተዋል።
አምባሳደር ደዋኖ ቻይና በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎትና ዝግጅት እንዳላት አረጋግጠዋል።
በኤምባሲው በኩል ተለይተው ግንኙነት የጀመሩ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በፋርማሲዩቲካልና በተለያዩ የማኑፋክቸሪግ ዘርፎች ገብቶ የመሳተፍ ፍላጎት መኖራቸው በመድረኩ ተመላክቷል።
የኮርፖሬሽኑ የማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘመን ጁነዲ ኮርፖሬሽኑ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ስላደረገውን ሪፎርም አብራርተዋል።
የውጭ ኢንቨስትመንትን አሟጦ ለመጠቀም ከባለድርሻ አካላት በተለይም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር የተጀመሩ ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያለመላክታል።