ቀጥታ፡

ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀት የሚያመርተው ፋብሪካ ከአንድ ወር በኋላ ስራ ይጀምራል -የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት 

አዲስ አበባ ሰኔ 2/2015(ኢዜአ)፦ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀት የሚያመርተው ፋብሪካ ከአንድ ወር በኋላ ስራ ይጀምራል ሲል የፌደራል አምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ የእንሰት ምርት ከምግብነቱ ባሻገር ተረፈ- ምርቱ ለመድኃኒት፣ ለእንስሳት መኖ እንዲሁም ለሌሎች አገልግሎቶች እንደሚውል ይታወቃል።

በተጨማሪ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከዘጠኝ ወራት በፊት ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀት መስራት እንደሚቻል በላብራቶሪ ማረጋገጡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሂደቱ አሁን ላይ ምን ደረጃ እንደደረሰ ለማወቅ በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የምርምርና ቴክኖሎጅ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑትን ዶክተር ዴሲሳ ያደታን ጠይቋል።

ዶክተር ዴሲሳ  በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢንስቲትዩት የእንሰት ተክል በስፋት በሚበቅልባቸው በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ በሲዳማ ክልል፣ በምዕራብ አርሲ ዞን፣ በምዕራብ ሸዋ ዞንና አብዛኛዉ ደቡብ ክልል ጥልቅ ምርምሮችን ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።

በዚህ የምርምር ወቅት የእንሰት ተረፈ ምርት ለወረቀት መስሪያነት እንደሚያገለግል በተግባር መረጋገጡን ገልጸዋል።

ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀት መስራት ከተረጋገጠበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ የግብርና ተረፈ ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ስራውን ለማስጀመር እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የማምረት ስራውን በተግባር ለማስጀመር ከሰው ሃይል ጀምሮ አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት ሙሉ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ከአንድ ወር በኋላ በአንድ የግብርና ተረፈ ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ  ወረቀት የማምረት ስራው በይፋ ይጀመራል ብለዋል።

በዚህም በአመት 5 ሺህ 116 ቶን ወረቀት ይመረታል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት ዶክተር ዴሲሳ በሂደት ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ወደ ውጪ የመላክ  እቅድ እንዳለ  ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ዴሲሳ ኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ 2017 እስከ 2021 ድረስ ለወረቀት መግዣ  ብቻ 360 ሚሊዮን  ዶላር ወጪ ማድረጓን በጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል።

በየአመቱም ወደ 100 ሚሊዮን  ዶላር ወጭ እንደምታደርግ አመላክተዋል።

በቀጣይ ስራ የሚጀመረው የወረቀት ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ የወረቀት አቅርቦትን በአገር ውስጥ በማሟላት የውጭ ምንዛሬ ፍላጎትን በእጅጉ እንደሚቀንስ ገልጸዋል።

ለወረቀት መስሪያ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው የፐልፕ ዛፍ ተክል ጥቅም ላይ ለማዋል በርካታ አመታትን እንደሚፈጅ ገልጸው፣ ለኢትዮጵያ ከእንሰትና ከሌሎች የግብርና ተረፈ ምርቶች ወረቀትን ማምረት አማራጩን እንደሚያሰፋው ተናግረዋል።

ቻይና ከግብርና ተረፈ ምርት ወረቀት አምርቶ ወደ ውጭ በመላክ በአለም ቀዳሚ ሀገር መሆኗን ለአብነት አንስተዋል።

በኢትዮጵያ 85 በመቶው ህዝቧ በግብርና የሚተዳደር መሆኑ ለዚሁ አላማ የሚውልን ተረፈ ምርት በብዛት  ለማግኘት እንደ መልካም አጋጣሚ ሊወሰድ ይገባል ነው ያሉት።

የወረቀት ምርቱን ማምረት የሚጀመረዉ ገላን በሚገኘዉ ባርጉባ ፋብሪካ ሲሆን በሒደትም በሌሎች ፋብሪካዎች እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ውጥኑ ከተማን ከገጠር በኢኮኖሚ ከማስተሳሰር በተጨማሪ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር በኩልም ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተመላክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም