በፕሪሚየር ሊጉ 28ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ

 

አዲስ አበባ ሰኔ 2/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።

አዳማ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ አዳማ ከተማ በ36 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና በ39 ነጥብ 4ኛ ደረጃን ይዟል።

አዳማ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በአንዱ ሲያሸንፍ፤ በሁለቱ ተሸንፎ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።


 

ተጋጣሚው ሀዲያ ሆሳዕና ካለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ፤ በአንዱ ሲሸነፍ በአንዱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል።


 

በሌላኛው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከሃዋሳ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰአት ያገናኛል።

ከሊጉ አስቀድሞ መውረዱን ያረጋገጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ12 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ የያዘ ሲሆን ሃዋሳ ከተማ በ38 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በአራቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።


 

ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ በበኩሉ ካለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አንዱን ሲያሸንፍ አራት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ትናንት በተደረጉ የ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ ድሬዳዋ ከተማን 3 ለ 1 እንዲሁም አርባ ምንጭ ከተማ ለገጣፎ ለገዳዲን 2 ለ 1 ማሸነፋቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም