በ2016 በጀት ዓመት ከጠቅላላ የካፒታል በጀት 68 ነጥብ 7 የሚሆነው ለመንገድ፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ግብርና እና ገጠር ልማት የውሃ ነባር ፕሮጀክቶች የተመደበ ነው - የገንዘብ ሚኒስትር - ኢዜአ አማርኛ
በ2016 በጀት ዓመት ከጠቅላላ የካፒታል በጀት 68 ነጥብ 7 የሚሆነው ለመንገድ፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ግብርና እና ገጠር ልማት የውሃ ነባር ፕሮጀክቶች የተመደበ ነው - የገንዘብ ሚኒስትር
አዲስ አበባ ሰኔ 1 / 2015(ኢዜአ) ፡- በ2016 በጀት ዓመት ከተመደበው ጠቅላላ የካፒታል በጀት ውስጥ 68 ነጥብ 7 የሚሆነው ለመንገድ፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ግብርና እና ገጠር ልማት የውሃ ነባር ፕሮጀክቶች የተመደበ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2016 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት የማስመዝገብ እቅድ መያዙም ተገልጿል።
በ6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 24ኛ መደበኛ ስብሰባ ምክር ቤቱን 23ኛ መደበኛ ቃለጉባኤ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
በዚሁ ስብሰባም የ2016 በጀት ዓመት ረቂቅ የፌደራል መንግስት በጀት መግለጫ ላይ ተወያይቶ ለፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፤ በጀቱ ሲዘጋጅ የተመሰረተባቸውን ኢኮኖሚያዊ ታሳቢዎችና የትኩረት ፕሮግራሞች በተመለከተ ለምክር ቤቱ በዝርዝር አቅርበዋል።
ለመደበኛ ወጪዎች 370 ነጥብ 14 ቢሊየን ብር፣ ለካፒታል ወጪዎች 203 ነጥብ 44 ቢሊየን ብር፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 214 ነጥብ 07 ቢሊየን ብር፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ደግሞ 14 ቢሊየን ብር መመደቡን አስረድተዋል።
የረቂቅ በጀቱ ሲዘጋጅ በ2016 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ7 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚገመት ጠቁመው፤ በጀቱም ይህንኑ ለማሳካት ለሚውሉ መሰረታዊ ወጪዎች እንዲውል ይሰራል ብለዋል።
ረቂቅ በጀቱ ሲዘጋጅ በመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ቁጥጥር እንደሚደረግ፣ የገንዘብ አቅርቦትን በመገደብም አሁን ያለውን ከፍተኛ የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
የ2016 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ጤናማ የፊስካል ፖሊሲን የማረጋገጥ አቅጣጫን ተከትሎ የተዘጋጀ ሲሆን ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሁለተኛው ምዕራፍ ጋርም የተጣጣመ ነው ብለዋል።
ለፌደራል መንግስት መደበኛ ወጪዎች ከተመደበው 369 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ውስጥ 63 ነጥብ 6 በመቶው ለሀገር ውስጥና ለውጭ ዕዳ ክፍያ፣ ለማዳበሪያ ድጎማ፣ ለአደጋ መከላከልና ለመጠባበቂያ ተደልድሏል።
ለካፒታል ወጪ ከተደለደለው 203 ነጥብ 44 ቢሊየን ብር 146 ነጥብ 1 ቢሊዮን የሚሆነው ከመንግስት ግምጃ ቤት፣ ከ31 ነጥብ 6 ቢሊዮን ከፕሮጀክቶች እርዳታ፣ 25 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ከፕሮጀክቶች ብድር እንዲሸፈን ተናግረዋል።
ለካፒታል ወጪዎች ከተመደበው ውስጥ 81 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆነው ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የተመደበ ሲሆን ከጠቅላላ የካፒታል በጀቱ 68 ነጥብ 7 የሚሆነው ለመንገድ፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ግብርና እና ገጠር ልማት የውሃ ነባር ፕሮጀክቶች የተመደበ ነው ብለዋል።
በጦርነት የተጎዱ መሰረተ ልማቶችንና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እና ማህበረሰቡን ለማቋቋም ከመንግስት ግምጃ ቤት 20 ቢሊዮን ብር መመደቡን ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም በዝርዝር በቀረበው የ2016 በጀት ዓመት ረቂቅ የበጀት መግለጫ ምላሽና ማብራሪያ ይሻሉ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ጥያቄና አስተያየት አቅርበዋል።
በጥያቄና አስተያየታቸውም ረቂቅ በጀቱ አዳዲስ የሰራተኛ ቅጥርና የልማት ፕሮጀክቶች እንዳይኖሩ ታሳቢ መደረጉ የህዝቡን የመልማት ጥያቄና የተማረ ዜጋን የስራ ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ እንዳልሆነ አንስተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በሰጡት ምላሽ በተቻለ መጠን አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ተጨማረ በጀት ማመንጨት ይጠይቃል ብለዋል።
በቀጣይ ከልማት አጋር የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የልማት ተቋማት ጋር በሚገኝ ገቢ የዋጋ ግሽበትን፣ መሰረታዊ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የፌደራል መንግስት ለ2016 በጀት ዓመት 801 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀት እንዲመደብ መወሰኑ ይታወቃል።