የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልበር ሸምሱ ከጅቡቲ የወደቦችና ነጻ ቀጠናዎች ባለስልጣን ሊቀ መንበር ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልበር ሸምሱ ከጅቡቲ የወደቦችና ነጻ ቀጠናዎች ባለስልጣን ሊቀ መንበር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ሰኔ 1/2015(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልበር ሸምሱ ከጅቡቲ የወደቦች እና ነጻ ቀጠናዎች ባለስልጣን ሊቀ መንበር ኦማር ሀዲ ጋር ተወያይተዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ የኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪዶር አስተዳደር ባለስልጣን ማቋቋም እንዲሁም ባለስልጣኑ የሚኖሩት ኃላፊነቶች እና ስራዎችን አስመልክቶ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልበር ሸምሱ የተመራ ልዑክ በጅቡቲ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛል።
የጉብኝቱ አላማ የኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪዶር አስተዳደር ባለስልጣን ለማቋቋም እና በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪዶር የተሳለጠ የድንበር ዘለል ስራዎች እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲኖር ለማድረግ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ምክክር ማድረግ መሆኑም ተገልጿል።