ቀጥታ፡

አገር አቀፍ የብስክሌት ውድድር በትግራይ ክልል ሊካሄድ ነው

መቀለ ሰኔ 01/2015 (ኢዜአ) አገር አቀፍ የብስክሌት ውድድር ከሰኔ 14 እስከ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በትግራይ ክልል ሊካሄድ ነው።

ውድድሩን አስመልክቶ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መግለጫ ሰጥተዋል።

መግለጫውን የሰጡት የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኽላይ ፍቃዱ ውድድሩን ለማካሄድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት ውድድሩ ከፊታችን ሰኔ 14 እስከ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በክልሉ መቀለ ከተማ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

በውድድሩ ከአገሪቷ ሁሉም አካባቢዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ ብስክሌተኞች ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ውድድሩ በሁለቱም ፆታ የሚካሄደ ሲሆን ውድድሩ በክልሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ከማነቃቃት ባለፈ የሕዝቡን እርስ በርስ ግንኙነት ከማጠናከር አንጻርም ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጽም ወልደአብ ጉዳዩን አስመልክቶ ለኢዜአ እንደተናገሩት አመታዊው የብስክሌት ውድድር በመቀሌ ይካሄዳል።

ውድድሩንም ፌዴሬሽኑ ከትግራይ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመሆን እንደሚያዘጋጅም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም