ቀጥታ፡

የምግብና መጠጥ ማቀነባበሪያና ማሸጊያ ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ይሰራል-የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

 አዲስ አበባ ሰኔ 1 / 2015(ኢዜአ) ፡- በኢትዮጵያ የምግብና መጠጥ ማቀነባበሪያና ማሸጊያ ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እንደሚሰራ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለፀ።

5ተኛው አግሪ ፉድ እና የምግብ ማሸጊያ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል። 
 

በንግድ ትርኢቱ መክፈቻ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድን ጨምሮ አምባሳደሮች፣ የንግዱ ዘርፍ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በንግድ ትርኢቱ ከተለያዩ አገራት የተወጣጡ ከ130 በላይ የንግድ ትርኢት አቅራቢዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ቻይና፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ፣ ሕንድ፣ ጣልያን፣ ተርኪዬ፣ ኦስትሪያ፣ ቡልጋሪያ ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ጆርዳን እና ኬንያ በንግድ ትርኢቱ የተሳተፉ የውጭ አገራት ናቸው።

የንግድ ትርኢቱ በግብርና፣ በምግብ ማቀነባበሪያ፣ ፕላስቲክ፣ ሕትመት እና የማሸጊያ ኢንዱስትሪ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የንግድ ትርኢቱ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጠቀሜታ አለው።

በተለይ ወቅታዊ የንግድ እድሎችን ለማወቅ እና በኢንዱስትሪው ውስጥ ስላሉ አዳዲስ ለውጦች በበቂ ሁኔታ ለመረዳት ጠቃሚ እድሎችን እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የምግብና መጠጥ ማቀነባበሪያና ማሸጊያ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ የምታስመጣ መሆኑንና ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በየአመቱ እንደምታጣ ነው የተናገሩት።

ይህን ሁኔታ ለመቀየር በ'ኢትዮጵያ ታምርት' ንቅናቄ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፤ ይህ የንግድ ትርኢት በምግብና መጠጥ ማቀነባበሪያና ማሸጊያ ቴክኖሎጂዎች ያሉ ልምዶችን ከየሀገራቱ ተሞክሮ አንፃር ለመቅሰም ያግዛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የምግብና መጠጥ ማቀነባባሪያና ማሸጊያ ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እየሰራች እንደምትገኝም ተናግረዋል።
 

የንግድ ትርኢቱ አዘጋጅ አቶ ነብዩ ለማ የግብርና ኢንዱስትሪውን በቴክኖሎጂ በማዘመን ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል ብለዋል።

በተለይ በቴክኖሎጂ ሽግግር አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት እሴት ጨምሮ ለማዘጋጀት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ የሀገራትን ተሞክሮ በመቀመር ወደ ስራ ለመግባት ያስችላል ነው ያሉት።

በንግድ ትርኢቱ ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙ ኩባንያዎች መካከል የጣሊያኑ ንግድ ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሪካርዶ ዙኮኒ የንግድ ትርኢቱ በኢትዮጵያ ገበያ ለመግባት በር ከፋች መሆኑን ተናግረዋል።
 

በተለይ በዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በርካታ እድሎች ያሉ በመሆናቸው በቀጣይ  ተሳትፏቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ሌላኛው የንግድ ትርኢቱ ተሳታፊ ጀማል መሀመድ በበኩሉ በኢንዱስትሪው ውስጥ ስላሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ለውጦች የልምምድ ልውውጥ ለማድረግ ይረዳል ብለዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆየውን የንግድ ትርኢት ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም