በሸገር ከተማ ከእምነት ተቋማት ጋር ተያይዞ የነበሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል- የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ ከእምነት ተቋማት ጋር ተያይዞ የነበሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል- የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት
አዲስ አበባ ሰኔ 01/2015 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ከእምነት ተቋማት ጋር ተያይዞ የነበሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከክልሉ መንግሥት ጋር የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ።
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ከክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ያደረገውን አጠቃላይ ውይይትና የተገኙ ውጤቶችን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ በመግለጫቸው የነበረው ውይይት ጠቃሚ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።
ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተደረገው ሰፊ ውይይት ውጤት የተገኘበትና በሰላም ዙሪያ በጋራ የምንሰራበትን መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ከእምነት ተቋማት ጋር ተያይዞ የነበሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን በከተማው ፕላን መሰረት ሕጋዊ የመስጅድ መሥሪያ ቦታ የሚሰጥ መሆኑንም ቃል ገብተውልናል ብለዋል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱን ሙሉ መግለጫ ያቀረቡት የፕሬዝዳንቱ የአደረጃጀትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ተጠሪ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል፤ ሕዝበ ሙስሊሙ ከተሞችን ለማዘመን የሚከናወንን ዕቅድ ይደግፋል ብለዋል።
የልማት ዕቅዶች ሲወጡ እና ሲተገበሩ ግን ሰው ተኮር ሆነው በመግባባትና በመነጋገር የሚፈጸሙ መሆን አለባቸው ነው ያሉት።
በተደረገው ውይይትና በተደረሰው መግባባት የሸገር ከተማ የሃይማኖት እሴትን መሰረት አድርጎ ለመገንባት መታቀዱ መልካም መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል።
ለቤተ-እምነቶች የግንባታ ቦታ የከተማዋን ፕላን መሰረት ባደረገ መልኩ ለመስጠት መታቀዱም በጥሩ መልኩ ተነስቷል።
በአገር ደረጃ ሊጠቀስ የሚችል ትልቅ መስጅድና ለእስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ መሬት ለመስጠት መታሰቡን በመግለጫው ጠቅሰዋል።
በጠቅላይ ምክር ቤቱ እና በክልሉ መንግሥት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሕዝበ ሙስሊሙ ትብብርና እገዛውን እንዲያጠናክር ጥሪ ቀርቧል።