የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2016 በጀት ዓመት የ7 ነጥብ 9 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል - ሚኒስትር አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2016 በጀት ዓመት የ7 ነጥብ 9 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል - ሚኒስትር አህመድ ሽዴ
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2015(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2016 በጀት ዓመት የ7 ነጥብ 9 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚገመት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 24ኛ መደበኛ ስብስባውን እያካሄደ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በስብሰባው ላይ የፌዴራል መንግስትን የ2016 በጀት ዓመት ረቂቅ የበጀት መግለጫ አቅርበዋል።
በመጪው በጀት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 7 ነጥብ 9 በመቶ እንደሚያድግ መተንበዩንና ረቂቅ በጀቱ የተዘጋጀው የአገሪቷ ኢኮኖሚ ከገጠሙት ቀውሶች ወደ መደበኛ እና ጤናማ ሁኔታ እንደሚመለስ ታሳቢ በማድረግ መሆኑን አቶ አህመድ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ የ6 ነጥብ 1 በመቶ እድገት እያስመዘገበ እንደሚገኝ እና በተያዘው በጀት ዓመትም የ7 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ይመዘገብታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
የቀጣዩ በጀት የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ መንግስት ሊወስዳቸው ያሰባቸውን ጥብቅ የገንዘብ እና ፊስካል ፖሊሲ እርምጃዎችን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የ2016 ረቂቅ በጀት የ281 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ የበጀት ጉድለት እንደታየበትም ነው የገንዘብ ሚኒስትሩ ያስረዱት።
በረቂቅ በጀቱ የፌዴራል መንግስት ለማግኘት ካቀደው 520 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 440 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብሩን ከታክስ ለመሰብሰብ ማቀዱን አብራርተዋል።
መንግስት ገቢውን ለመሰብሰብ ያለውን አቅም በሙሉ አሟጦ መጠቀምን መሰረት ያደረገ አማራጭ እንደሚከተል አስገንዝበዋል።
ምክር ቤቱ በቀረበው የበጀት ረቂቅ ላይ ከተወያየ በኃላ፤ ረቂቅ የበጀት አዋጁን ለዝርዝር እይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይመራል ተብሎ ይጠበቃል።