የትምህርት ቤቶች የፈጠራ ውጤቶች ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት መሠረት የሚጥሉ በመሆኑ አስፈላጊው ድጋፍና እገዛ ይደረጋል- የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈጉባኤ

439

አዲስ አበባ ሰኔ 1/2015 (ኢዜአ)  የትምህርት ቤቶች የፈጠራ ውጤቶች ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት መሠረት የሚጥሉ በመሆኑ አስፈላጊው ድጋፍና እገዛ የሚደረግ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ቡዜና አልከደር ገለጹ።

8ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎችና የመምህራን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ አውደ-ርዕይ
“በሳይንስ ቴክኖሎጂ ፈጠራ የዳበረ ትውልድ ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ በወዳጅነት ፓርክ ተከፍቷል፡፡ 


 

በአውደ-ርዕዩ ላይ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችና መምህራን የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ይዘው ቀርበዋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ቡዜና አልከድር፤ አውደ-ርዕዩ የፈጠራ ውጤቶች የሚተዋወቁበት፣ ተወዳዳሪነት የሚጎለብትበትና የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት መሆኑን ገልጸዋል።

በተማሪዎችና መምህራን የሚቀርቡ የፈጠራ ሥራዎች ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የአውደ-ርዕዩ መዘጋጀት ፈጠራን ለማስፋፋትና ፈጣሪዎችን ለማበረታታት የላቀ ትርጉም አለው ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የፈጠራ ሥራዎቹ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲያድጉ የሚጠበቅበትን እገዛና ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የሳይንስና ፈጠራ ሥራን መሠረት በማስያዝ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥም የትምህርት ቤቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው፤ በአዲሱ ሥርዓተ-ትምህርት ትኩረት ከተሰጠባቸው ዘርፎች መካከል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በመሆኑም ተማሪዎች በንድፈ-ሀሳብ የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን እንዲያቀርቡ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በትምህርት ቤቶች የኤሌክትሮኒክ ትምህርት (ኢ-ስኩል) ለማጠናከር የሚያስችል የመሰረተ-ልማት ዝርጋታ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

የተማሪዎችን የሳይንስ ምርምር ሥራ ማስተዋወቅ የሚጀመረው በቤተ-ሙከራና በትምህርት ማበልጸጊያ ማዕከላት በመሆኑ ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ትምህርት ቤቶች ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

በዛሬው እለት በይፋ የተከፈተው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ አውደ-ርዕይ መልካም ጅማሮ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በወዳጅነት አደባባይ በዛሬው እለት የተከፈተው ከተማ አቀፍ የተማሪዎችና የመምህራን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ አውደ-ርዕይ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም