የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከ114 ሄክታር በላይ ቦታ በአረንጓዴ ልማት የማስዋብ ስራ መስራቱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከ114 ሄክታር በላይ ቦታ በአረንጓዴ ልማት የማስዋብ ስራ መስራቱን አስታወቀ
ባህርዳር ሰኔ 01/2015 (ኢዜአ) የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በሁሉም ግቢዎቹ ከ114 ሄክታር በላይ የሚሆን ቦታ በአረንጓዴ ልማት በማስዋብ ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር መቻሉን አስታወቀ።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የግቢ ውበት ዳይሬክተር ዶክተር ደሴ አሰፋ እንደገለጹት ግቢዎቹን የማስዋብና ጽዱ የማድረግ ስራው በዩኒቨርሰቲው መልካም የመማርና ማስተማር ስራ መፍጠር እያስቻለ ነው።
በዩኒቨርሲቲው በሁሉም ግቢዎቹ ክፍት ቦታዎች ላይ የነበረውን ቆሻሻ በማጽዳት፣ በመመንጠርና በመደልደል ከ114 ሄክታር በላይ ቦታ በአረንጓዴ ልማት በማስዋብ ጽዱ የማድረግ ስራ መሰራቱን ነው የገለጹት።
ግቢዎቹን የማስዋብ ስራው እየተከናወነ የሚገኘውም ዲዛይን በማሰራትና ለአረንጓዴ ልማቱ የሚያገለግሉ አትክልት፣ አበባና የሳር ዝርያዎችን በመጠቀም መሆኑን አስረድተዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ ልማትና የማስዋብ ስራው በዓመት እስከ 22 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ ማከናወን መቻሉን አስገንዝበዋል።
በአረንጓዴ ልማትና በማስዋብ ስራው፣ የለማውን አካባቢ በመንከባከብና በሌሎች ተያየዥ ዘርፎች አሁን ላይ ከ12ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስራ አጥ ወገኖች የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ ልማት ስራውም አሁን ላይ በግቢው ንጹህና ነፋሻ አየር በመፍጠር ለመማር ማስተማር፣ ለጥናትና ምርምርና እንዲሁም ሌሎች ስራዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
ይህ መልካም የአረንጓዴ ልማት ጽዳትና ውበት ጥበቃ ስራም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አቢይ አህመድ እውቅና የተሰጠው መሆኑን አውስተዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ 46 ዩኒቨርሲቲዎችም የተሰራውን የአረንጓዴ ልማት ስራ መጥተው በመጎብኘት ያገኙትን ተሞክሮ በመውሰድ እየተገበሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የ4ኛ ዓመት የሳይኮሎጅ ተማሪ የሆነችው መቅደስ ተሻገር በበኩሏ የምንማርበት ግቢ አረንጓዴ ልማት የተሰራለት ጽዱና ውብ በመሆኑ የውጭ መዝናኛ እንጂ መማሪያ ግቢ አይመስለም ብላለች።
ይህም እኛ ተማሪዎች አብዛኛውን ጊዜያችን በመማር፣ በማጥናትና በመፈተን በማሳለፍ የተጨናነቀውን አእምሯችን ወደ ለማው አካባቢ በመሄድ ተዝናንተን አእምሯችን አንድናድስ እድል ፈጥሮልናል ብላለች።
ሌላዋ የ3ኛ ዓመት የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ተማሪ ውብአለም ተፈራ እንዳለችው የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ግቢውን በማሳመር የሰራው ስራ ለሌሎች ድርጅቶች አርአያ የሚሆን ነው ብላለች።
ግቢያችን ላይ የተሰራው የአረንጓዴ ልማትና መዝናኛ ቦታዎች ሳንጨናነቅ እንድናነብና ሌሎች ስራዎችን በመስራት በውጤታችን ስኬታማ እንድንሆን እያስቻለን ነው ብላለች።