የሽብር ቡድኖች በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም ዳግም እንዳያንሰራሩ በጋራ አቅምን ማስተባበር ያስፈልጋል -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
የሽብር ቡድኖች በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም ዳግም እንዳያንሰራሩ በጋራ አቅምን ማስተባበር ያስፈልጋል -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2015(ኢዜአ):- የሽብር ቡድኖች በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም ዳግም እንዳያንሰራሩና የግንኙነት መስመራቸው እንዲቋረጥ በጋራ መስራት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለማጥፋት እየተደረገ ባለው ዓለም አቀፍ ጥረት ላይ የጸና አቋም አላትም ብለዋል።
'አይ ኤስ አይ ኤስ' የሽብር ቡድንን ለማጥፋት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ጥምረት የሚኒስትሮች ስብስባ ዛሬ በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ እየተካሄደ ነው።
በስብስባው ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እየተሳተፉ ነው።
ማለዳ ላይ በነበረው ስብስባ የጥምረቱ አባል አገራት ተወካዮች በየአገራቸው 'አይ ኤስ አይ ኤስ'ን ጨምሮ ሌሎች የሽብርተኛ ቡድኖችን ለመዋጋት ያላቸውን ቁርጠኝነት አስመልክቶ አጭር ገለጻ አድርገዋል።
በመድረኩም ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ ሽብርተኝነትን እየተዋጋች እንደምትገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
አል-ሻባብ የንጹሃን ዜጎችን ሕይወት በመቅጠፍ እና የዕለት ተዕለት ኑሯቸው ላይ መስተጓጎል በመፍጠር ለምስራቅ አፍሪካ እና ለተቀረው ዓለም ስጋት ሆኖ መቀጠሉን አመልክተዋል።
የሽብር ቡድኖች በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም ዳግም እንዳያንሰራሩ፣ እንዳይስፋፉና የእርስ በርስ የግንኙነት መስመራቸውን ለመቁረጥ የጋራ አቅም እና ኃይል ማስተባበር በጣም ቁልፍ የሆነ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ቡድኖች በአገራት ላይ የሚያደርሱትን ስቃይ መጋራት እንደሚገባ ነው አቶ ደመቀ ያስገነዘቡት።
ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን ለማጥፋት እየተደረገ ባለው ዓለም አቀፍ ጥረት ላይ የጸና አቋም እንዳላት ገልጸዋል።
'አይ ኤስ አይ ኤስ' የሽብር ቡድንን ለማጥፋት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ጥምረት ኢትዮጵያን ጨምሮ 85 አባል አገራት እንዳሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ጥምረቱ የሽብርተኞች ሰንሰለትን ማጥፋት እና መበጣጠስ፣ የቡድኖቹን ፕሮፖጋንዳ ማክሸፍ፣ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው የሽብር ቡድን ተዋጊዎች ድንበር ተሻግረው ጥቃት እንዳያደርሱ መከላከል፣ የሽብር ቡድኖች ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸው የሚጠቀሙባቸውን መሰረተ ልማቶች ላይ ከባድ ጉዳት በማድረስ አቅማቸውን ማዳከምን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ሽብርተኝነትን የመዋጋት ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ገልጿል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከስብሰባው ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ውይይቶች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።