ቀጥታ፡

በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ስጋት የደቀነውን የብረት ጣሪያ ለማንሳት የሃይድሮሎጂና ጂኦ ቴክኒካል ጥናቶች ሊካሄዱ ነው- የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን

አዲስ አበባ ሰኔ 01/2015 (ኢዜአ) በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ስጋት የደቀነውን የብረት ጣሪያ ለማንሳት ከተጀመሩ ጥናቶች ባሻገር መሰረታዊ የሃይድሮሎጂና ጂኦ ቴክኒካል ጥናቶችን ለማካሄድ  የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ።

በ1970 ዓ.ም በመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የላሊበላ የውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካነ ቅርስ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ስነ ጥበባዊ አበርክቶና ዋጋው የላቀ መሆኑ ይነገራል።

የኢትዮጵያ አስደናቂ የኪነ ህንጻ ጥበብ መገለጫ የሆነውና ዘጠኝ ምዕተ ዓመታት ያስቆጠረው የላሊበላ መካነ ቅርስ በ2000 ዓ.ም በጊዜያዊነት የተሰሩ የቅርሱ የብረት መጠለያዎች ከተቀመጠላቸው የአገልግሎት ዘመን በላይ በመቆየታቸው  በቅርሱ ላይ ስጋት መፍጠራቸው በተደጋጋሚ ተነስቷል።

በመሆኑም የብረት ጣሪያዎች በቅርሱ ላይ የሕልውና ስጋት በመደቀናቸው በጥንቃቄ እንዲነሱ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል።


 

የቅዱስ ላሊበላ 11ዱም አብያተ ክርስቲያናት ካህናት አለቃ ሊቀ ካህናት አበበ ኃይሌ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ለአምስት ዓመታት ተብሎ ለቅርሶች መከላከያ የተሰራው የብረት ጥላ 15 ዓመታት በማስቆጠሩ ካህናትና ነዋሪዎች ዛሬም ስጋታቸው ጨምሯል።  

የቅዱስ ላሊበላ ደብር ሰበካ ጉባዔ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጌጡ ወዳጆ በበኩላቸው፤ የላሊበላና አካባቢው ህዝብ በዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት' የተጀመሩ መካነ ቅርሱን የመጠበቅና የልማት ስራዎች ቢኖሩም ህዝቡ በሰላማዊ ሰልፍ ሳይቀር የጠየቀው የመጠለያዎች ይነሱልኝ ጥያቄ ግን ዛሬም አልተመለሰም ብለዋል።


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የላስታ ላሊበላ አካባቢ ህዝብ ተወካይ ቅድስት አርዓያ፤ የህዝቡ ትልቁ ስጋት የብረት ጣሪያዎች ጉዳይ በመሆኑ፤ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡት ጠይቀዋል። 


 

 የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ኃይሉ፤ በቅርሶች ላይ ያለውን መጠለያ ከማንሳት ጋር ተያይዞ ተጓዳኝ ጉዳቶች እንዳይኖሩ በቅድሚያ መሰረታዊ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህም ከዚህ በፊት ከተደረጉ ጥናቶች በተጨማሪ የስነ ውሃና የስነ ምድር (Hydrological and Geological Stduy) ቴክኒካዊ ጥናቶችን ማካሄድ የሚያስችል የጥናት ጨረታ ለመክፈት ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።


 

በጉዳዩ ላይ ህዝቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ከአካባቢው ተወላጆችና ከህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት ስለመደረጉ አንስተዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው፤ የህዝቡ በቅርሶች ላይ የተሰራው ጣሪያ ይነሳልን ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጣሪያ ማንሳቱ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያመጣ በጥናት መደገፍ ስላለበት መዘግየቱን ተናግረዋል።

በዚህም በዩኔስኮ ፈቃድ መሰረት በዚህ ትውልድ የማያዳግም መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በማንሳት፤ በፈረንሳይ መንግስት በተገኘ 5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ጥናቶች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ጥናቱ ሲጠናቀቅም ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ ጉዳት ሳያደርስ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚሰጠው ነው የተናገሩት።

በአፄ ላሊበላ ዘመነ መንግስት ከአንድ ወጥ ዓለት ተፈልለው የተሠሩ 11 የላሊበላ ውቅር አብያተክርስትያናት ቤተ መድሃኒአለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ ሚካኤል፣ ቤተ መስቀል፣ ቤተ ጎልጎታ (ደብረ ሢና)፣ ቤተ ደናግል፣ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ መርቆርዮስ፣ ቤተ ገብርኤል ሩፋኤል፣ አባ ሊባኖስ እና ቤተ ጊዮርጊስ ናቸው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም