ቀጥታ፡

ለዘመናት በጽኑ መሠረት ላይ ተገንብቶ የዘለቀው የኢትዮጵያና ሩስያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጠንካራ ወዳጅነት ሁነኛ ማሳያ ነው- የቀድሞ ሶቪየት ሕብረት ተማሪዎች

አዲስ አበባ ሰኔ 1/2015(ኢዜአ):- ለዘመናት በጽኑ መሠረት ላይ ተገንብቶ የዘለቀው የኢትዮጵያና ሩስያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጠንካራ ወዳጅነት ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የቀድሞ ሶቪየት ሕብረት ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ገለጹ።

በባህልና ስነ-ጽሑፍ ጥልቅ መሰረት ያለው የኢትዮ-ሩስያን ዘመን ተሻጋሪ ወዳጅነት በፖለቲካና ምጣኔ ኃብት ረገድም ይበልጥ ማጠናከር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ከአንድ ምዕተ-ዓመት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያና ሩስያ ወዳጅነት በመልክዓ-ምድር ርቀት ሳይወሰን፣ በዘመናት ውጣውረዶች ሳይበገር እስካሁንም የዘለቀ መሆኑ ይታወቃል።

በዚሁ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቀድሞ ሶቪየት ሕብረት ተማሪዎች ሩሲያ በቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አገራት ነፃነት በመደገፍ እና የነፃ ትምህርት ዕድል በመስጠት ሊዘነጋ የማይችል ውለታ አላት ብለዋል።

የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት ተማሪ የነበሩት አንጋፋው ደራሲና ሃያሲ አያልነህ ሙላቱ፤ በታሪክ ዘውዳዊ ሥርዓት መመራታቸው፣ ኦርቶዶክስ ሃይማኖታትና የአሌክሳንደር ፑሽኪን ማንነት ለሀገራቱ ቁርኝነት ሰበብ ሆኗል ይላሉ።

ሩስያ በታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ በማይናወጥ አቋም ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን አጋርነቷን ያሳየችና አሁንም አብራ የዘለቀች ወዳጅ አገር መሆኗን ጠቅሰው፤ ለኢትዮጵያ የላቀ አገልግሎት ያላቸውን በርካታ ምሁራን በማስተማር ተጠቃሽ መሆኗን ገልጸዋል።

በቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት ለስድስት ዓመታት በዓለም አቀፍ ሕግ የተማሩት አንጋፋው ዲፕሎማት በላይ ግርማይ፤ በዘመነ ደርግና በዘመነ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ወክለው 12 ዓመታት አገልግለዋል።

የተማሪነት ዘመናቸውን ጨምሮ በድምሩ ለ18 ዓመታት በሩሲያ መኖራቸውን ጠቅሰው "ሩስያ ሁለተኛ ሀገሬ ነች" የሚሉት አቶ በላይ፤ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር ሩስያ ዘመን የማይሽራት አጋር ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

በደርግ ዘመን ሩስያ ከተማሩ 27 ሺህ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ የሆኑት አለማየሁ አሊ፤ ትምህርታቸው እርሻ ቢሆንም በሩስያ የስነ-ጽሑፍ ፍቅር "ተለክፌያለሁ" ይላሉ።

በተለይም ከአፄ ምንሊክ ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያን ነፃነት የደገፈችና ተቋማትን ያቋቋመች ወዳጅ አገር መሆኗን ገልፀዋል።

በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከሩስያ ስነ-ጽሑፍ ነገረ-አመክንዮ፣ ፍልስፍና፣ ስነ-ልቦና፣ የሳይንስ ዕውቀቶችን መቋደሳቸውን ጠቅሰዋል። 

በርካታ የኢትዮጵያ ስነ-ጽሑፍ ሥራዎችም ወደ ሩስያኛ እና የሩስያኛ መጻህፍትንም ወደ አማርኛ መተርጎማቸውን አስታውሰው፤ ለአብነትም በ1870ዎቹ በግዕዝ የተጻፉ ሰዓታት የተሰኘውን የዜማ መጽሐፍ ወደ ሩስያኛ መተርጎሙን አንስተዋል። 

በሞስኮ ትምህርት ቤቶች የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት እንዲሰጥ መወሰኑን ሩስያዊያን ለኢትዮጵያዊያን ያላቸውን አክብሮት  ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።

ከሦስት ዓመታት በፊት በነፃ ትምህርት ዕድል የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በሞስኮ ያጠናቀቁት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ ሚካኤል ጅማ፤ የሩስያ ነፃ የትምህርት ዕድል አሁንም መቀጠሉን ያነሳሉ።

በየዓመቱ ቢያንስ ለ20 የዩኒቨርሲቲ መምህራን የትምህርት ዕድል እንደምትሰጥ ገልፀው፤ በመጪው አዲስ ዓመትም ለሦስተኛ ዲግሪ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ ሩስያ እንደሚያቀኑ ገልጸዋል።

በጽኑ መሠረት ላይ ተገንብቶ ለዘመናት የዘለቀው የኢትዮጵያና ሩስያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጠንካራ ወዳጅነት ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የቀድሞ ተማሪዎቹ ገልጸዋል።

ሩስያ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመው፤ በባህልና ስነ-ጽሑፍ ጥልቅ መሠረት ያለው ዘመን ተሻጋሪ ወዳጅነት በፖለቲካና ምጣኔ ኃብት ረገድም ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኢያቭጌኒ ተርኪን፤ ሩስያና ኢትዮጵያ በዘመናት እና በመንግሥታት መለዋወጥ የማይናወጥ በመተማመንና መደጋገፍ ላይ የተመሰረተ ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው አገሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጋራ ጥቅምና በመተማመን ላይ የተመሰረተው የሁለቱ  ሀገራት ግንኙነት፣ ኢኮኖሚና ሰብዓዊ እርዳታን ጨምሮ በብዙ መስኮች መጠናከር ያለበት እንደሆነ ያምናሉ።

ኢትዮጵያዊ የዘር ማንነት ያለው ሩስያዊ ባለቅኔ አሌክሳንደር ፑሽኪን የኢትዮጵያና ሩስያን ሕዝቦች የባህል፣ የመንፈስና የስሜት ቅርበት ነጸብራቅ እንደሆነም አንስተዋል።

የሁለቱን ሀገራት ዘመን አይሽሬ ወዳጅነት በምንም ነገር ሳይበገር ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም