በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ770 ሺህ በላይ የውጭ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል--ቱሪዝም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ770 ሺህ በላይ የውጭ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል--ቱሪዝም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2015(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የመጣውን ሰላም ተከትሎ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ770 ሺህ በላይ የውጭ ቱሪስቶች ለጉብኝት መምጣታቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ለአብነትም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ770 ሺህ በላይ የውጭ ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን የጠቀሰው ሚኒስቴሩ ለዚህም የሰላም ስምምነቱ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማምጣቱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ጦርነትና የኮቪድ ወረርሽኝን ጨምሮ በተፈጥሯዊና በሰው ሰራሽ ችግሮች ተቀዛቅዞ ቆይቷል፡፡
በዚህም ምክንያት የዘርፉ አገልግሎት ሰጪዎች ገቢ መቀነስ፣ የጎብኝዎች ቁጥር ማሽቆልቆልና ሌሎችም ችግሮች የተስተዋሉ ሲሆን ሀገሪቱም ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንድታጣ አድርጓታል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዘርፉ በተጋረጠበት ፈተና የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ በማድረጉ ይገኝ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ገድቦት ቆይቷል፡፡
በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት በሀገሪቱ ገጽታ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳረፉ ባሻገር በዘርፉ የሚፈጠሩ የስራ ዕድሎች እንዳይኖሩ ጫና አሳድሮ እንደነበር አስታውሰዋል።
መንግሥትና ህወሓት ለሁለት ዓመታት የቆየውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ማድረጋቸው ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱም ተዳክሞ የነበረው የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃና ወደ ነበረበት እንዲመለስ የሚያደርግ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቱሪዝም ሚኒስቴርም የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ዘርፉን ለማነቃቃትና ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በሀገሪቱ ሰላም መስፈኑን ከማስተዋወቅ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰዋል።
የዘርፉ አገልግሎት ሰጪዎችና ሚኒስቴሩ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻሉን ተናግረዋል።
ለአብነትም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ770 ሺህ በላይ የውጭ ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
የውጭ ጎብኝዎች ቁጥር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱን በማንሳት ለዚህም የሰላም ስምምነቱ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።
ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተጀመረው የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት የቱሪዝም ፍሰቱን ለማጠናከር እንደሚያግዝ በመጠቆም ሚኒስቴሩም ለስኬታማነቱ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም በጦርነት አውድ የቆዩ የሆቴልና ሌሎች የዘርፉ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጎብኝዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት እንዲያደርጉ ስልጠናን ጨምሮ ሌሎችም ድጋፍና ክትትሎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
በትግራይ ክልል የሚገኙ የቱሪዝም ሃብቶችን በማስተዋወቅ እና የአገልግሎት ፓኬጆችም እንዲሸጡ በማድረግ ረገድ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ቱሪዝም ዘርፉን በዘላቂነት በውጤታማነት በማስቀጠል ሁሉን አቀፍ ትብብር የሚጠይቅ መሆኑንም ተናግረዋል።