ቀጥታ፡

በአፋር ክልል የ13 ወረዳዎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው

ሰመራ ሰኔ 01 /2015 (ኢዜአ)፡-በአፋር ክልል በሚገኙ 13 ወረዳዎች በርካታ የቤተሰብ አባላትን ተጠቃሚ የሚያደርግ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሠመራ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ እንደገለፁት የጤና መድህን ስርዓቱ በወረዳዎቹ መጀመር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ከሚጀምሩት 13 ወረዳዎች በተጨማሪ በሰባት ወረዳዎች ለመጀመር የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ በበኩላቸው በአፋር ክልል የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል እየተሰራ ያለውን ስራ አድንቀዋል።


 

የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎትን በክልሉ ባሉ ወረዳዎች ማስጀመር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ መርሃ ግብሩ በትክክል እንዲተገበር የአመራሩ ክትትልና ቁጥጥር አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ከአርብቶ አደሩ የሚሰበሰበው ገንዘብ በትክክል ለታለመለት አላማ መዋሉን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የማህበረሰብ የጤና መድህን አገልግሎት ህብረተሰቡ የህክምና አገልግሎት ወጪ ሳያሳስበው ተጠቃሚ የሚሆንበት በመሆኑ ቀሪ ወረዳዎችም እንዲጀምሩ ለማድረግ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

በአፋር ክልል ከዚህ ቀደም 15 ወረዳዎች የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም