የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2015(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።
በመርሐ-ግብሩ መሰረት አርባ ምንጭ ከተማ ከለገጣፎ ለገዳዲ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።
አርባ ምንጭ ከተማ በ30 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኝ ሲሆን አስቀድሞ ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ለገጣፎ ለገዳዲ በ15 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አርባ ምንጭ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አንዱን ሲያሸንፍ አራት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ተጋጣሚው ለገጣፎ ለገዳዲ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በሶስቱ ሲሸነፍ በአንዱ አቻ ወጥቷል።
አርባ ምንጭ ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ በጊዜያዊነት ከወራጅ ቀጠና የመውጣት እድል ያገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መጠናቀቁ ይታወሳል።
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሁለተኛ ጨዋታ በወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከተማ መካከል ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ይደረጋል’።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ወላይታ ድቻ በ33 ነጥብ 13ኛ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ በ36 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ወላይታ ድቻ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ ሲሸነፍ በሶስቱ ነጥብ ተጋርቷል።
ድሬዳዋ ከተማ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ተሸንፏል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ወላይታ ድቻ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር እስከ ሰኔ 4 2015 ዓ.ም ይቆያል።
ከ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በተጨማሪ ከነገ በስቲያ የ26ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ-ግብር በዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ መካከል ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ይደረጋል።
ጨዋታው በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ግንቦት 18 2015 ዓ.ም መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በከባድ ዝናብ ምክንያት ሜዳው ማጫወት ባለመቻሉ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሞ ነበር።
የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የውድድር እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ጨዋታው በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስታዲየም እንዲደረግ መወሰኑ ይታወቃል።
በተስተካካይ ጨዋታው ምክንያት በ28ኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና ሊያደርጓቸው የነበሩ ጨዋታዎች ሰኔ 18 2015 እንደሚከናወኑ ኮሚቴው አስታውቋል።
በተጨማሪም ከ28ኛ እስከ 30ኛ ሳምንት ያሉ የሊጉ ጨዋታዎች በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደሚደረጉ አመልክቷል።
የ29ኛ እና 30ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቀንና ሰአት የቡድኖችን ውጤት መሰረት በማድረግ ሊቀየር እንደሚችልም የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር ውድድር እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ገልጿል።