ቀጥታ፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ልዑክ በቻይና የሚገኘውን የዳግዚንግ ነጻ ንግድ ቀጣና እና ልዩ ኢኮኖሚክ ዞንን ጎበኘ

አዲስ አበባ ሰኔ 1/2015(ኢዜአ):- የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ልዑክ በቻይና የሚገኘውን የዳግዚንግ ነጻ ንግድ ቀጠና እና ልዩ ኢኮኖሚክ ዞንን ጎብኝቷል።

ነጻ ንግድ ቀጣና እና ልዩ ኢኮኖሚክ ዞኑ በቻይና ከሚገኙ ግዙፍ የኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት ቦታዎች መካከል የሚጠቀስ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ አመልክቷል።

ልዑኩ በጉብኝቱ የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጣናን ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዙ ልምዶች፣ አሰራሮችና የአሰራር ስርዓቶችን መመልከቱ ተገልጿል።

ዳግዚንግ ነፃ ንግድ ቀጣና እና ልዩ ኢኮኖሚክ ዞን በፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ ተመርቆ ወደ ስራ የገባ ሲሆን በሚሰጠው አገልግሎትና ስፋት ከቤጂንግ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ የበለጠ አየር ማረፊያ በውስጡ የያዘ መሆኑ ተመላክቷል።

ቻይናን ከመላው ዓለም ጋር ይበልጥ በኢኮኖሚ እንደሚያስተሳሰር የተገለጸው ዓለም አቀፍ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ ዞን ቤጂንግን ጨምሮ ፣ ቲያንጂን እና ሁቤይ ከተሞችን እንደሚያካትት ተጠቁሟል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግ እና ኮሙኒኬሽን መምሪያ ከሌሎች የኮርፖሬሽኑ የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በቻይና ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም