በግሪክ የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ላይ በወንጀል ጥርጣሬ በደረሰ ጥቆማ ምርመራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በግሪክ የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ላይ በወንጀል ጥርጣሬ በደረሰ ጥቆማ ምርመራ ተጀመረ
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2015 (ኢዜአ ) በአዲስ አበባ በግሪክ የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ላይ በወንጀል ጥርጣሬ በደረሰ ጥቆማ ምርመራ መጀመሩን የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።
የትምህርት ሂደቱ እንዳይስተጓጎል አዲስ አስተዳደር ተሹሞ ሥራ መጀመሩም ተገልጿል።
ፍትሕ ሚኒስቴር የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ቦርድና አስተዳደር ከተለያዩ ወንጀሎች ጋር ተያይዞ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በደረሰ ጥቆማ መሰረት የወንጀል ምርመራ መጀመሩን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በወንጀል የተገኘ ኃብት ምርመራና ማስመለስ ዳይሬክተር ጄነራል ጸጋ ዋቅጅራ፤ በግሪክ የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ላይ የወንጀል ምርመራ መጀመሩን ገልጸዋል።
የወንጀል ምርመራው የተጀመረው የቀድሞ ቦርድና አስተዳደር በወንጀል ድርጊት ተሳትፈዋል በሚል በመጠርጠራቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የተለያዩ የወንጀል ጥርጣሬዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ከዚህ መካከል በወንጀል የተገኘ ኃብት እንዳይሸሽ ለማድረግ ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል።
ለጊዜው መጠኑ ያልታወቀ ከፍተኛ ገንዘብ በወንጀል ድርጊት ተገኝቷል የሚል ጥርጣሬ በመኖሩ፤ ገንዘቡ ወደ ተለያዩ አካላት እንዳይሸጋገር፣ በትምህርት ቤቱና በማኅበረሰቡም ላይ ጉዳት እንዳይደርስና ለሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች አስተዳደር መሾሙን ተናግረዋል።
አዲስ የተሾመው አስተዳደር በሙስና ወንጀል ልዩ ሥነ-ሥርዓት ሕግ 434/1993 አዋጅ መሰረት ለፍትሕ ሚኒስቴርና ለፖሊስ በተሰጠ ሥልጣን መሰረት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የተሾሙት አስተዳዳሪዎች ንብረቱን በጊዜያዊነት ተረክበው የወንጀል ክስና ምርመራው ተጠናቆ የመጨረሻ ውሳኔ በመዝገቡ እስኪገኝ ድረስ ንብረት እንዲጠብቁና እንዲያስተዳድሩ መሾማቸውን ነው ያስረዱት።
አስተዳዳሪዎቹ ንብረቶቹን ከማስተዳደር ባሻገር የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዳይስተጓጎል ትምህርት ቤቱን እንዲመሩ ከቀድሞ የትምህርት ቤቱ ቦርድ ሥራ መረከባቸውንም ገልጸዋል።
ለግሪክ ትምህርት ቤት ጊዜያዊ አስተዳደር ሆነው ከተሾሙት መካከል ጌታቸው ተፈራ፤ አዲሱ አስተዳደር ከትላንት ጀምሮ ሥራውን ጀምሯል ብለዋል።
በቀጣይም ከትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብና ከወላጆች ጋር ውይይቶች የሚደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።