ቀጥታ፡

በአገሪቷ ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲገነባ የዴሞክራሲ ተቋማት የጀመሩትን ሥራ ማጠናከር አለባቸው- ቋሚ ኮሚቴው

ሀዋሳ ግንቦት 30/2015  (ኢዜአ) በአገሪቷ ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲገነባ የዴሞክራሲ ተቋማት የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። 

ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሀዋሳ ጽህፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሀዋሳ ቅርጫፎችን ጨምሮ የዴሞክራሲ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴን ለመገምገም የመስክ ምልከታ አድርጓል።

የቋሚ ኮሚቴው ቡደን መሪ ወይዘሮ ዘሀራ ቢፍቱ በእዚህ ወቅት እንዳሉት መንግስት በአገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት እየተጠናከረ እንዲመጣ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው። 

ጠንካራ የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዲገነባ በማድረግ በኩል የዴሞክራሲ ተቋማት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው በእዚህ ረገድ የጀመሩትን ሥራ እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።   

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሀዋሳ ጽህፈት ቤት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት በመስራት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም ለመከላከል እያከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል። 


 

በሲዳማ ክልል በማረሚያ ተቋማትና በፖሊስ ጣቢያዎች ያለውን ሰብአዊ መብት አያያዝን ተዘዋውረው ማየታቸውን የተናገሩት ቡድን መሪዋ፣ በጉብኝቱም ከታራሚዎች የሰብአዊ መብት አያያዝ አንጻር አመርቂና የተሻሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በመስክ ምልከታው የመብት ጥሰቶች እንዳልተፈጸሙ በተጨባጭ ማረጋገጣቸውንም እንዲሁ።

በኮሚሽኑ የሀዋሳ ጽህፈት ቤት ያለውን አሰራርና አደረጃጀት በተመለከተ በአካል ተገኝተው ከተመለከቱት በተጨማሪ ሥራዎቹን በሪፖርቱ ቀርበው መገምገማቸውንም ወይዘሮ ዘሀራ ገልጸዋል።

በእዚህም በጥንካሬ የታዩትን ጽህፈት ቤቱ እንዲያጠናክርና የተወሰኑ ክፍተቶቹንም በቀሪ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲያሟላ ምክረሀሳብ መሰጠቱን አመልክተዋል።   

ጽህፈት ቤቱ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ከተለያዩ አካላት ጋር ተቀራርቦ በመስራት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም ለመከላከልና ተፈጽሞ ሲገኝም ለማጣራት እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ወይዘሮ ዘሀራ አሳስበዋል።

በኮሚሽኑ የሀዋሳ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ በጋሻው እሸቱ በበኩላቸው እንዳሉት ሰብዓዊ መብቶችን የማስጠበቅ ሥራ የኮሚሸኑ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ባለድርሻ አካላት ቅንጅትን የሚጠይቅ ነው።

ቅንጅታዊ አሰራር የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም ቀድሞ ለመከላከልም ሆነ ተፈጽሞ ሲገኝ በፍጥነት ለማጣራት የሚሰራውን ሥራ ውጤታማ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአካል ተገኝቶ የጽህፈት ቤቱን አሰራር በመገምገም የሰጠው ድጋፍ የኮሚሽኑ ምክረ ሀሳብ ተፈጻሚ እንዲሆን ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አስታውቀዋል። 

ቋሚ ኮሚቴው በተጨማሪም በሀዋሳ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሲዳማና ደቡብ ክልሎች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤትና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሀዋሳ ማስተባበሪያን የሥራ እንቅስቃሴን ተመልክቷል። 

ወይዘሮ ዘሀራ በእዚህ ወቅት እንዳሉት የሚዲያ ተቋማቱ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን፣ እንዲሁም በመንግስት የሚከናወኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ የሚያከናውኗቸው ተግባራት መልካም ናቸው።

በመንግስት የተሰሩ ሥራዎችንና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ለህብረተሰቡ ከማድረስ ባለፈ የህዝቡን ችግር  ለመንግስት በማሳወቅ አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚመጣ በተቋማቱ የሚሰሩ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ ብቸኛና አንጋፋ የሆው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ካለው የብዙ ዓመታት ልምድና ከሚያቀርባቸው ጥራት ያለው መረጃ ተአማኒነቱ የተሻለ እንደሆነም ወይዘሮ ዘሀራ ገልጸዋል። 

በየአካባቢው ባሉ ቅርንጫፎቹ ከመረጃ ተደራሽነት ባለፈ ተሞክሮ የሚሆኑ ተግባራት ማየታቸውንም ጠቁመዋል።

"ኢዜአ እያከናወናቸው ያሉ የለውጥ ሥራዎች እጅግ አበረታች ናቸው" ያሉት ወይዘሮ ዘሀራ፣ በቀጣይ አቅሙን በማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።


 

ወይዘሮ ዘሀራ እንዳሉት ሁለቱም የሚዲያ ተቋማት በእውነተኛ ምንጭ ላይ የተመሰረተ መረጃን በወቅቱ ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ በአሁኑ ወቅት ባልተገባ መንገድ በማህበራዊ ሚዲያ የሚነዙ የሀሰት ወሬዎችን መመከት ይገባቸዋል።


 

በእዚህ ረገድ ሁለቱም ተቋማት የሚያከናውኗቸውን ተግባራት በቀጣይ አጠናክረው እንዲቀጥሉም አስገንዝበዋል።

ተቋማቱ ሥራዎቻቸውን በሚፈለገው ልክ ማከናወን እንዲችሉ ከሰው ሀይልና ከግብአት ጋር የሚስተዋሉ ውስንነቶች እንዲሟላ መስራት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

 

 

 

 

 

 

 

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም