ለምግብነት የሚውሉ ምርቶችን ደህንነት የማረጋገጥ ስራ ላይ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል-የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
ለምግብነት የሚውሉ ምርቶችን ደህንነት የማረጋገጥ ስራ ላይ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል-የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2015(ኢዜአ)፦ ለምግብነት የሚውሉ ምርቶች ከማምረት ጀምሮ ለተጠቃሚው እስከሚደርስ ያለውን ደህንነት የማረጋገጥ ስራ ላይ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።
ዓለም አቀፍ የምግብ ደህንነት ቀን በኢትዮጵያ ለአራተኛ ጊዜ ˝የምግብ ደረጃዎች ህይወትን ያድናሉ ˝በሚል መሪ ቃል ተከበሯል።
በዕለቱም በኢትዮጵያ የምግብ ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ ያለውን ነባራዊ ሁኔታና አለማቀፍ ተሞክሮዎችን የሚያሳይ መነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ የምግብን ደህንነት መጠበቅ የሚያስገኘውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ላይ ዜጎች ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ በማለም በየዓመቱ ግንቦት 30 የዓለም የምግብ ደህንነት ቀን እንዲሆን ማድረጉን ገልፀዋል።
ዓላማውም በዓለም አቀፍ ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚወጡ ደረጃዎች የምግብን ደህንነት እና ጥራት ከማስጠበቅ አንጻር ያላቸውን ፋይዳ ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመስጠት ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።
ባለስልጣኑ የምግብ ምርቶችን ደህንነት ከማረጋገጥ አንጻር በተለያዩ ጊዜያት የቁጥጥር ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የ91 የምግብ ምርት ዓይነቶች የጥራት መስፈርትን አሟልተው ባለመገኘታቸው ለምግብነት እንዳይውሉ ተደርጓል።
ለምግብነት እንዳይውሉ ከተከለከሉ ምግቦች መካከል ጨው፣ የምግብ ዘይት፣ የለውዝ ቅቤ፣ አቼቶና ሌሎችም ተጠቃሾች ናቸው።
በተጨማሪም 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቶን የሚሆኑ ልዩ ልዩ ምግቦች ላይ ጥራትና ደህንነታቸውን በመፈተሽ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን ገልፀዋል።
ዳይሬክተሯ አያይዘውም በርካታ የምግብ አይነቶች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው በማለፉ እና በሚጓጓዙበት ወቅት ባገጠማቸው መበላሸት 13 ሺህ 428 ቶን የምግብ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ ባለስልጣኑ ለምግብነት የሚውሉ ምርቶች ደህንነት ለማረጋገጥ የሚሰራውን ስራ ሊያግዙ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሀሚድ ጀማል በበኩላቸው ደህንነታቸውና ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምግቦች ሰዎችን ለጤና መታወክ እንዲሁም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንንም ችግር ለመፍታት የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ብሎም የእንስሳት ተዋጽኦ ውጤቶችን በማምረት ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ፣አርብቶ አደሮችና አምራቾች ለህብረተሰቡ ምርታቸውን ከማድረሳቸው በፊት በአመራረት ሂደት ውስጥ ሊወስዱ የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታ ትኩረት ሊሰጡበት ይገባል ብለዋል።
የምግብ ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የህግ ማእቀፎች እና አሰራሮችን ማሻሻል እንዲሁም አዳዲስ ህጎችን የማውጣት እና በሀገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።