የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ ወሳኝ እርምጃ በመሆኑ መደገፍና መስፋት አለበት- አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ ወሳኝ እርምጃ በመሆኑ መደገፍና መስፋት አለበት- አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ ወሳኝ እርምጃ በመሆኑ መደገፍና መስፋት እንዳለበት በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ገለጹ።
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት በአራት ዓመት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከትል የሚያስችል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብርን በሐምሌ 2011 ዓ.ም በይፋ መጀመሯ ይታወቃል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብሮች ሕዝብን በማሳተፍ ከተያዘው ዕቅድ በላይ በማሳካት 25 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።
ዘንድሮ በሚካሄደው አምስተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብርም ለምግብ የፍራፍሬ ተክል፣ ለንግድ ደን ልማት እና ለእንስሳት መኖ የሚውሉ ዝርያዎችን ጨምሮ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በዓለም አቀፋዊ ምሳሌነት የሚነሳና የሚደነቅ እርምጃ ነው።
ሩሲያ ኢኒሼቲቩን በመደገፍ ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ መርሐ-ግብሮች በእንጦጦ እና በኤምባሲዋ ውስጥ ችግኝ በመትከል መሳተፏን ጠቅሰዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፋዊ ችግር በመሆኑ የጋራ መፍትሔ እንደሚያሻው ጠቅሰው፤ "በተለይ ያደጉ አገራት ተጨባጭ ውጤት ከሌላቸው እንቅስቃሴዎች ወጥተው በቁርጠኝነት ትርጉም ያለው እርምጃ ሊወስዱ ይገባል" ብለዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስና ችግሩን ለመቋቋም ትርጉም ያለው ዓለም አቀፋዊ እርምጃ በመሆኑ ሁሉም ሊደግፈውና ሊያስፋፋው እንደሚገባ ነው አምባሳደር ኢቭጌኒ ያመለከቱት።
አሁናዊ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የሰው ልጆች የወደፊት ዘላቂ ሕይወትን የሚወስኑ በመሆናቸው በዘመቻው መሳተፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌሎች የአፍሪካ አገራትም እንደ የአገራቱ ዐውድ እና ችግኝ የመትከል ልምድ ከአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ተሞክሮ ሊወስዱ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ላደረጉት አስተዋጽኦ በአሜሪካ የስኬት አካዳሚና የዓለም አቀፍ ተስፋ ጥምረት ምርጥ የአፍሪካ አመራርነት ሽልማትን በታህሳስ ወር 2015 ዓ.ም መሸለማቸው የሚታወስ ነው።