በቦረና ዞን በኤልወዬ ወረዳ 642 ሄክታር መሬት የእንስሳት መኖ ሳር ለምቶ ለአጨዳ ደርሷል - ኢዜአ አማርኛ
በቦረና ዞን በኤልወዬ ወረዳ 642 ሄክታር መሬት የእንስሳት መኖ ሳር ለምቶ ለአጨዳ ደርሷል
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2015(ኢዜአ):-በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በኤልወዬ ወረዳ በሳሪቴ ቀበሌ በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት 642 ሄክታር መሬት በተፈጥሮ የእንስሳት መኖ ሳር ለምቶ ለአጨዳ መድረሱ ተገለጸ፡፡
መኖው ከ1 ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ትስሰር ገጹ ባሰፈረው መረጃ አመልክቷል።
በቦረና ዞን የነበረውን ቁጥቋጦ የፕሮጀክቱ ባለሙያዎች በማስተባበር በአርብቶ አደር ጉልበት በመመንጠር፣ አካባቢውን ከሰውና ከእንስሳት ንኪኪ በመጠበቅና ዝናብ ሲዘንብ ለእንስሳት መኖ የሚሆን የሳር ዘር በመዝራት ምርቱን ማግኘት መቻሉን ተጠቁሟል።
በፕሮጀክቱ ኤልወዬ ወረዳ አስተባባሪ አቶ ታለን ዱለቻ እንዳሉት የለማው የእንስሳት መኖ በአርብቶ አደሩ እንደሚታጨድ እና በዚህም 100 ሺህ እንስሳት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
በድርቁ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኦሮሚያ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የመሰረታዊ አገልግሎት ማሻሻያና አቅም ግንባታ ኦፊሰር ወይዘሮ ባንቻዬ ኢታና ሳሩ በወቅቱ ታጭዶ በመጋዘን በማከማቸት እጥረት ሲያጋጥም ቀስ በቀስ ጥቅም ላይ እንደሚውል አመልክተዋል።
አርብቶ አደሩ በአጨዳ ስራው ላይ በንቃት እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል።
የግጦሽ ፕሮጀክቱ በ2013 በጀት ዓመት መጀመሩንና አሁን ላይ ውጤት እየታየበት እንደሚገኝ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ከ64 ሺህ ሄክታር በላይ የግጦሽ ሳር በተፈጥሯዊ ዘዴ በዝናብ ማልማት መቻሉን አመልክቷል።