በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ90 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የጥራ ጥሬ ሰብሎች ይለማሉ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ90 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የጥራ ጥሬ ሰብሎች ይለማሉ
አዳማ ግንቦት 30/2015 (ኢዜአ):- በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ90ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የጥራ ጥሬ ሰብሎች በመኸር እርሻ እንደሚለሙ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለፀ።
የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የጥራ ጥሬ ሰብል ለማልማት በትኩረት እየተሰራ ነው።
ከ11 የዞኑ ወረዳዎች አብዛኞቹ ቆላማና ወይናደጋማ የአየር ንብረት ያላቸው በመሆኑ ለጥራ ጥሬ ሰብል ልማት የተመቸ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በ2015/16 የመኸር እርሻ ከ90 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ጥራ ጥሬ ለመሸፈን የማሳ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል።
ቦሎቄ፣ ማሾና አኩሪ አተር ደግሞ በዋናነት ከሚለሙ የጥራጥሬ ሰብሎች መካከል መሆናቸውን የገለፁት አቶ መስፍን፤ ከዚህ ውስጥ ቦሎቄ ብቻ 64ሺህ ሄክታር ላይ ለማልማት መታቀዱን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ማሾ 20 ሺህ ሄክታር እንዲሁም አኩሪ አተር 5 ሺህ ሄክታር ላይ ለውጭ ገበያ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በእስካሁኑ ሂደትም ከ6ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት በጥራ ጥሬ ሰብል ዘር መሸፈኑንም አመልክተዋል።
ሁሉንም የውጭ ገበያ የጥራ ጥሬ ሰብል በሜካናይዜሽንና በኩታ ገጠም ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ አብዛኛው መሬት በሜካናይዜሽን ታርሶ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ የቦሎቄ ምርጥ ዘር ከህንድ በማስመጣት ከአካባቢው አየር ጋር በማላመድ ተስማሚነቱ ተረጋግጦ ለአርሶ አደሩ የተሰራጨ ሲሆን፤ የዘር ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዘር የተሸነፈው አካባቢ የቦሎቄ፣ የማሾና አኩሪ አተር ቡቃያዎቹ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በልማቱ ተሳታፊ ከሆኑት የዞኑ ወረዳዎች መካከል የአዳሚ ቱሉ ጂዱ ኮምቦልቻ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገመዶ ጤሶ በሰጡት አስተያየት በዘንድሮው የመኽር እርሻ ልማት ከስንዴና በቆሎ በተጨማሪ ጥራጥሬን ለውጭ ገበያ ለማምረት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በወረዳው በተለይም ቦሎቄን፣ አኩሪ አተርና ማሾን ለማምረት የሚመች ስነ ምህዳር ያለው በመሆኑ በዚህ ዘርፍ አርሶ አደሩን ስኬታማ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግም የአርሶ አደሩን ማሳ አንድ ላይ በማሰባሰብ በኩታ ገጠም እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ የሜካናይዜሽን እርሻ አገልግሎት አርሶ አደሩ በበቂ ሁኔታ እንዲያገኝ የእርሻ ትራክተሮች በአነስተኛ ዋጋ ክራይና ቅድመ ክፍያ በማስከፈል በብድር እንዲያገኝ መደረጉን ጨምረው ገልጸዋል።
ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች አንድ ላይ ተደራጅተው ቦሎቄን ለውጭ ገበያ እያለሙ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአዳሚ ቱሉ ጂዱ ኮምቦልቻ ወይሶ ቀንጨራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ወርቁ ኤዳኦ ናቸው ።
18 ሞዴል አርሶ አደሮች አንድ ላይ በመሆን 400 ሄክታር መሬት ላይ ቦሎቄና አኩሪ አተር ለማልማት በሜካናይዝድ የእርሻ ማሳ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።