ቀጥታ፡

ለኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል- ጤና ሚኒስቴር

ሐዋሳ ግንቦት 29/2015 (ኢዜአ) የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭቱን በሚፈለገው ልክ ለመቀነስ የስርጭት ምጣኔው ከፍተኛ በሆኑባቸው አካባቢዎችና ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በትኩረት እንዲሰራ የጤና ሚኒስቴር አስገነዘበ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ በዘርፉ እየታየ ያለው መዘናጋት አምራች የሆነው ወጣት እያሳጣ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ አሳስቧል።

በጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር የ2015 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ፕሮግራሞች ስራ አፈጻጸም በሃዋሳ እየገመገመ ነው።

በሚኒስቴሩ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚው አቶ ፈቃዱ ያደታ በዚህ ጊዜ እንደተናገሩት የኤች አይ ቪ/ ኤድስን ስርጭት ለመግታት ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ በልዩ ትኩረት የሚደረገው ርብርብ መጠናከር አለበት።

ባለፉት ዓመታት የኤች አይ ቪ/ ኤድስን ስርጭት በመከላከልና በመቆጣጠር የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ጫና ለመቀነስ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚታየው መዘናጋት በየዓመቱ ከ11 ሺህ በላይ ዜጎች በኤች አይ ቪ/ ኤድስ እንዲሞቱ ምክንያት  መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ከ8 ሺህ 350 በላይ የሚሆኑ ዜጎችም በየዓመቱ በአዲስ መልክ በኤች አይ ቪ/ ኤድስ እየተያዙ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ ብለዋል።

ከነዚህም ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ወጣቶችና ሴቶች መሆናቸውን በማመላከት።

እንደ ሃገር ያለው የስርጭት ምጣኔ 0 ነጥብ 86 በመቶ ቢሆንም፣ በተለያዩ አከባቢዎች የስርጭት ምጣኔው የተለያየ መሆኑን አንስተዋል። 

ለአብነትም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች፣ በሐረሪና ጋምቤላ ክልሎች የስርጭት ምጣኔው ከሁለት በመቶ በላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ሴተኛ አዳሪዎች፣ የረዥም ርቀት አሽርካሪዎችና የቀን ሠራተኞች ደግሞ ለኤች አይ ቪ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ስርጭቱን በሚፈለገው ልክ ለመቀነስ የስርጭት ምጣኔው ከፍተኛ በሆኑባቸው አካባቢዎችና ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በትኩረት መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።

''ሃገራዊው የስርጭት መጠን መቀነስ ሊያዘናጋን አይገባም'' ያሉት መሪ ስራ አስፈጻሚው፣ የስርጭት መጠኑ ከፍተኛ በሆኑባቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በጥናት የተደገፈ አገልግሎት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ 

ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ኢላማ ያደረገ ፈጣንና አዲስ የምርመራ ስልት ተቀይሶ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተው፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኤች አይ ቪ/ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያደርጉ አገልግሎቶችን በማጠናከር ውጤታማ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።


 

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰላማዊት መንገሻ በበኩላቸው ኤች አይ ቪ/ኤድስ የሕዝብ ጤና ችግር ተብለው ከተለዩ በሽታዎች አንዱ በመሆኑ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በክልሉ የማህበረሰቡንና የአጋር ድርጅቶችን ድጋፍና ተሳትፎ በማጠናከር ሃገራዊውን ተልእኮ ለማሳካት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤናና ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ በበኩላቸው በዘርፉ እየታየ ያለው መዘናጋት አምራች የሆነውን ወጣት እያሳጣ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

እንደ ሃገር የሚታሰበውን ብልጽግና ለማረጋገጥ ከሃገሪቱ ህዝብ 70 ከመቶ በላይ የሆነውን ወጣት ኃይል ከኤች አይ ቪ/ ኤድስ መጠበቅና መከላከል ይገባል ብለዋል።

ምክር ቤቱ በዘርፉ እየታየ ያለውን መዘናጋት ለማስቀረት የቁጥጥርና ክትትል ስራውን ከማጠናከር ባለፈ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ቋሚ ኮሚቴው የሚከታተላቸው ሌሎች ተቋማትም በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ዶክተር ከይረዲን፣ በትምህርት ተቋማት ላይ የሚሰሩ ስራዎች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመድረስ እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።

በመድረኩ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን፣የስራ አፈጻጸማቸውን አቅርበው ውይይት እየተደረገበት ነው።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው የአፈጻጸም መድረክ በቀጣይ አቅጣጫዎችና በዘርፉ በሚከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም