የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ብዝሃ ቋንቋ በማጎልበት ረገድ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል - የኮሚሽኑ ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ

1424

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2015(ኢዜአ)፡-  የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ብዝሃ ቋንቋ በማጎልበት ረገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኮሚሽኑ ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ፔድሮ ተናገሩ።

የሩስያ ቋንቋ ዓለም አቀፍ ቀን የመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ፔድሮ እና  በኢትዮጵያ የሩስያ ፌደሬሽን አምባሳደር ይቭጌኒ ተርክሂን ጨምሮ በርካታ እንግዶች በተገኙበት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተከብሯል።


 

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ስራ ጸሀፊ አንቶኒዮ ፔድሮ፤ የቋንቋ ቀን ከሰው ልጆች ባህል፣ ሥልጣኔ፣ ሰብዓዊነትና ሉዓላዊነት ጋር የተጣጣመ ነው ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥራ ቋንቋ የሆነው የሩስያ ቋንቋ ቀን በመላው ዓለም ባሉ የመንግስታቱ ድርጅት ቢሮዎች እንደሚከበርም ገልጸዋል፡፡

የሩስያ ቋንቋ ቀን የሩስያ ዘመናዊ ሥነ-ጽሁፍ አባት ተብሎ ከሚወደሰውና አፍሪካዊ ማንነት ከሚጋራው ዕውቁ ባለቅኔ አሌክሳንደር ፑሽኪን ልደት ጋር በማስተሳሰር የሚከበር ቀን መሆኑም ገልፀዋል።

ከ350 ሚሊየን በላይ ተናጋሪዎች ያሉት ሩስያኛ ቋንቋ በተለይም ምስራቅ አውሮፓና ማዕከላዊ ኤስያ ቀጣና በስፋት የሚነገር መሆኑን ገልጸዋል።

በትርጉም ቋንቋነቱ በዓለም አራተኛ እንዲሁም በኢንተርኔት መረጃ ምንጭነቱ በዓለም ላይ ሁለተኛ ደረጃ እንደሚይዝ ገልጸው፤ ይህም ለመንግስታቱ ድርጅት የስራ ቋንቋ እንዲሆን አስችሎታል ነው ያሉት። 

በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለብዝሃ ቋንቋ ዕድገት ከአጋር አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በኮሚሽኑ ቤተ መፃሕፍት የአሌክሳንደር ፑሽኪን ክፍል መደራጀቱንና በቋንቋ ማዕከሉ የሩስያ ቋንቋ ትምህርት ለመስጠት ከአዲስ አበባ ከሚገኘው የሩስያ ሳይንስና ቋንቋ ማዕከል ጋር በትብብር እንደሚሰራም ገልፀዋል።


 

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርክሂን፤ ዕለቱ ብዝሃ ቋንቋና ብዝሃ ባህልን ለማስፋፋት እንደሚከበር ገልጸው፤ የቋንቋ ቀን ሲከበርም ከሰው ልጆች ማንነት፣ ሥልጣኔዎችና ቅርሶች ዐውድ አንፃር የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል።

በአንዳንድ አካላት ቋንቋን ፖለቲካዊ መልክ የማስያዝ አካሄዶች መኖራቸውን ጠቅሰው ሩስያኛ ቋንቋም በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት ችግሮች የገጠሙት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቀኑን እንዲከበር በማድረጉ የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 

የሩስያ ቋንቋና ዕውቀትን ለኢትዮጵያዊያንና በኢትዮጵያ ለሚኖሩ የሌሎች አገራት ዜጎች ለማስፋፋትም በአዲስ አበባ የፑሽኪን የሳይንስና ባህል ማዕከል እየተሰራ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።

በአፍሪካ ደረጃ የሩስያ ቋንቋን ለማስተዋወቅም ከሀገራት ጋር በኢኮኖሚ፣ በትምህርትና ቋንቋ እንዲሁም በቱሪዝም መስኮች  ሁሉን አቀፍ ትብብሮች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በአውሮፓውያኑ 2010 የሩሲያ ቋንቋ በየዓመቱ እንዲከበር ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአዲስ አበባ በሚገኘው የኮሚሽኑ አዳራሽ በየዓመቱ ይከበራል።   

የመንግሥታቱ ደርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ደግሞ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2018 ጀምሮ ቀኑን በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበረ ቀጥሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም