የ 'ሲቲ ኔት' ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2015(ኢዜአ)፦ ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግበት የተገለጸው የ 'ሲቲ ኔት' ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማት ተግባራዊ መሆን ሊጀምር ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ እና ኢትዮ- ቴሌኮም ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የቢሮው ኃላፊ አቶ ሰለሞን አማረ እና የቴሌኮም ኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ናቸው።

የስማርት ሲቲ ፕሮጀክትን ተግባራዊ በማድረግ የመዲናዋ ነዋሪዎች በከተማ አስተዳደሩ ስር ባሉ ተቋማት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ  ለማድረግ ስምምነቱ መፈረሙን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።

ለዚህም በየተቋማቱ የኔትወርክ መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ እና መተግበሪያዎች የማበልጸግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂው ከፍተኛ ፍጥነት ያለው መሰረተ ልማት በመሆኑም ተቋማቱ አገልግሎታቸውን ለማዘመንና ቀልጣፋ ለማድረግ እንደሚረዳቸው ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ በመዲናዋ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ስር በሚገኙ 58 ተቋማት እና በ120 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል።

ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግበት ፕሮጀክት በአራት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው አቶ ሰለሞን የጠቆሙት።

'ሲቲ ኔት' ቴክኖሎጂ የከተማዋን ግብር አሰባሰብ፣ የወሳኝ ኩነት ምዝገባን ጨምሮ የቅሬታና አቤቱታ አቀራረብ ስርዓቶችን ለማዘመን የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ መዲናዋን የሚመጥን ዘመናዊ የሆኑ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎች እንዲኖሩ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ይኸው ፕሮጀክት በመዲናዋ የስማርት ሲቲ መርሐ-ግብርን እውን ለማድረግ ከተያዙት እቅዶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ስምምነቱ በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ የተለያዩ ቢሮዎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከዋናው የዳታ ማዕከል ጋር በቀላሉ ለማስተሳሰር የሚያስችል ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ተመሳሳይ አገልግሎቶችን በአንድ ጊዜ በማከናወንና የአሰራር ስርአትን በማዘመን አስተማማኝ፣ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም