ቀጥታ፡

በሽታን ተቋቁሞ የተሻለ ምርት የሚሰጥ የቡና ዝርያ እያስፋፋ መሆኑን የጅማ ግብርና ምርምር ማእከል ገለፀ

ጅማ ግንቦት 29/2015(ኢዜአ) ፡-በሽታን ተቋቁሞ የተሻለ ምርት የሚሰጥ የቡና ዝርያን እያስፋፋ መሆኑን የጅማ ግብርና ምርምር ማእከል ገለጸ።

በቡናና ሻይ ባለስልጣን የተመራ ቡድን የጅማ የግብርና ምርምር ማእከል ያገኛቸውን በሽታን መከላከል የሚችሉ የቡና ዝርያዎችን ጎብኝቷል።

በዚሁ ወቅት እንደተገለጸው ማዕከሉ በሽታን መቋቋም የሚችል እና የተሻለ ምርት የሚሰጥ የቡና ዝርያዎችን በምርምር በማግኘት የአርሶ አደሩን የቡና ምርታማነት ለመጨመር እየሰራ ነው።

በጅማ ግብርና ምርምር ማእከል የባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ክፍል አስተባባሪ ሀብታሙ ስዩም በማእከሉ በምርምር የወጣው የቡና ዝርያ በሽታን የሚቋቋም እና ምርታማነቱም የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዚህም በትንሽ ቦታ በርካታ የቡና ችግኞችን ማዘጋጀት መቻሉን የገለጹ ሲሆን ዝርያውን ለማባዛትም ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

በማእከሉ በ'ቲሹ ካልቸር' ምርምር የተገኘ የቡና ዝርያ ይፋ ማድረጉን ገልጾ በቀጣይ ዝርያውን አባዝቶ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም አንድ የቡና ዝርያን በማዳቀል ዝርያን ለማሻሻል እስከ 20 አመት ይፈጅ እንደነበረ ገልጸው አሁን በ'ቲሹ ካልቸር' በመጠቀም የተሻሉ የተዳቀለ ቡና ዝርያዎችን በአጭር ጊዜ ማግኘት ተችሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኤሲሞ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ የግብርና አሰራሮችን ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በሀገራችን የቡና በሽታን መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎችን በማውጣት እና የተሻሉ ዝርያዎችን በምርምር በመለየት የቡና ምርታማነት እንዲጨምር ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል።

የ'ቲሹ ካልቸር' ቴክኖሎጂ ከቡናው ቅጠል ወይም ሌላ የቡና አካል ክፍል አንዱን በመውሰድ የሚደረግ የምርምር ግኝት ሲሆን በጅማ ምርምር ማእከልም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ  በጅማ ግብርና ምርምር ማእከል በ'ቲሹ ካልቸር' የተዳቀለውን በሽታ መከላከል የሚችል የቡና ዝርያ ለማስፋፋት ይሰራል ብለዋል።

የተገኘውን የቡና ዝርያ በስፋት አባዝቶ በመጠቀም የተሻለ ምርትና ለማምረት እንዲቻል የበለጠ መስራት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም