ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ዩኤን ሀቢታት መርሃ-ግብር ጋር ያላትን ትብብር እና አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ ነች--የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር

1012

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መንግስት ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ሰፈራ መርሃ-ግብር (UN-Habitat) ጋር ያለውን ትብብር እና አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

"ለተሻለ የከተማ ዕድገት!" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ የሚገኘውን ጉባኤ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በይፋ ከፍተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልዑክ በኬንያ ናይሮቢ እየተካሄደ በሚገኘው ሁለተኛው የዩ ኤን ሃቢታት ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

የልዑኩ መሪ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን በመድረኩ ኢትዮጵያ በዘርፉ እያከናወነች ያለችውን ተግባራት በተመለከተ ማብራሪያ አቅርበዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በንግግራቸው የኢትዮጵያ መንግስት በከተማ ሴክተር እያከናወናቸው ያሉ ዋና ዋና የፖሊሲ መዋቅራዊ ለውጦችን ገልጸዋል።

አዲሱ የከተማ አጀንዳ እና የልማት ግቦችን በከተሞች ዘርፍ በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ከዩ ኤን ሃቢታት ጋር ያለውን ትብብር እና አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ጉባኤው እስከ ሰኔ 2/2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥል ከከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም