በአዲስ አበባ የሚገነቡ ትላልቅ ፕሮጀክቶች መዲናዋ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነቶችን በብቃት እንድትወጣ የሚያስችሏት ናቸው--ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የሚገነቡ ትላልቅ ፕሮጀክቶች መዲናዋ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነቶችን በብቃት እንድትወጣ የሚያስችሏት ናቸው--ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ግንቦት 29/2015(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የሚገነቡ ትላልቅ ፕሮጀክቶች መዲናዋ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነቶችን በብቃት እንድትወጣ የሚያስችሏት መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በአዲስ አበባ የሚገነባውና አህጉራዊው "ዊንዶው ኦፍ አፍሪካ" ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ተጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ግንባታውን ከሚያከናውነው ከቻይናው ፈርስት ሃይዌይ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ የኢትዮጵያ ኃላፊ ዊ ችያንግ ዩ ጋር በመሆን የፕሮጀክቱን ግንባታ ለማስጀመር የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል።
አጠቃላይ ፕሮጀክቱ የሚገነባው በ84 ሄክታር መሬት ላይ ሲሆን የመጀመሪያው ምዕራፍ በ14 ነጥብ 5 ሄክታር ላይ እንደሚገነባ ተገልጿል።
የግንባታ ወጪው በግልና በመንግሥት አጋርነት ማዕቀፍ የሚፈጸም ሲሆን፤ ቻይና ፈርስት ሃይወይ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ በ18 ወራት ውስጥ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ስራውን መረከቡ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ የአፍሪካውያን ባህል፣ ታሪክና መሰል ጉዳዮች የሚንጸባረቁበት የአፍሪካ ሙዚየም የሚያካትት ሲሆን የህጻናት መዝናኛ ቦታዎች፣ አረንጓዴ ሥፍራዎች፣ የመኖሪያ አፓርታማዎች፣ ባለ አምስትና ሦስት ኮከብ ሆቴሎችም ይገኙበታል።
ከንቲባ አዳነች በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ የሚገነቡ ትላልቅ ፕሮጀክቶች መዲናዋ ያሉባትን አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነቶች በብቃት ለመወጣት የሚያችላት ነው።
በገበታ ለሸገር የተገነቡ ፓርኮችና የወንዝ ዳር ልማቶች በአጭር ጊዜ መሳካት መንግስት ቃል የገባቸውን የልማት ስራዎች በአግባቡ እየፈጸመ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በአፍሪካውያን ስም የተሰየሙ ፓርኮችና ጎዳናዎች እንደነበሩ አስታውሰው፤ ሆኖም አፍሪካውያን ባህላቸውን እና ታሪካቸውን የሚያንጸባርቁበት ቦታ እንዳልነበራቸው ገልጸዋል።
"ዊንዶው ኦፍ አፍሪካ" ፕሮጀክት በዚህ ረገድ የሚታየውን ክፍተት የሚሞላ ለአፍሪካም ኩራት የሚሆን ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ደቦ ቱካ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ ግንባታ በአምስት ምዕራፍ ተከፍሎ የሚከናወን መሆኑን አብራርተዋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ የሆነው ዛሬ መሰረተ ድንጋዩ የተጣለው ብቻ 14 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባ ሲሆን ሰው ሰራሽ ሃይቆች፣ ፋውንቴኖች፣ የሰርግ ሥነ ስርዓት የሚካሄድባቸው ቦታዎችና የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች እንደሚኖሩት ጠቅሰዋል።
ግንባታው በተሻለ ጥራትና በሚጠበቀው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።
የቻይና ፈርስት ሃይዌይ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ የኢትዮጵያ ኃላፊ ዊ ቺያንግ ዩ እንደተናገሩት፤ ኩባንያው ወዳጅነት አደባባይ፣ፑሽኪን አደባባይና የጎተራ ማሳለጫ መንገድ ግንባታን በተሳካ መንገድ አከናውኗል።
የዊንዶው ኦፍ አፍሪካ ፕሮጀክት ግንባታንም በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ የሚያስችለውን ሙሉ ዝግጅት ማድረጉንም አብራርተዋል።