የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅትና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በጋራ ለመሥራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅትና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በጋራ ለመሥራት ተስማሙ
አዲስ አበባ ግንቦት 29/2015(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት እና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ መብራት እና የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ተፈራርመዋል።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ መብራት እንዳሉት፤ ድርጅቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የጥራት ሽልማት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዛሬውም ስምምነት አገልግሎቱ መድኃኒትን በጥራት ለሕዝብ እንዲያደርስ የሚያግዝ ነው።
በዚህም መሠረት በአገልግሎቱ ዋና መሥሪያ ቤትና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መካከል የጥራት ሽልማት ማካሄድ፣ ለአገልግሎቱ ሠራተኞችና አመራሮች ሥልጠና መስጠት እና የማማከር ሥራዎችን እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የአገሪቱን ተወዳዳሪነት ለማሳደግና ጥራት በአገሪቱ ባህል እንዲሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም ከጥራትና ከልህቀት ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን ለተለያዩ ድርጅቶች በመስጠት ጥራት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅቶች የሚሰጡትን አገልግሎት በተሻለ ጥራት እንዲሰጡ እና ውጤታማ ሥራ እንዲሰሩ ለማስቻል እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ውድድር በማዘጋጀት ለአሸናፊዎች እውቅና እና ሽልማት እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፤ የመግባቢያ ስምምነቱ አገልግሎቱ ለኅብረተሰቡ ጥራት ያላቸውና ፈዋሽነታቸው የተጠበቀ መድኃኒት ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ የሚደረገውን ተግባር የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጤናማ ሕብረተሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ለመስጠት ያስችላልም ብለዋል።
ስምምነቱ የአገልግሎት እና መድኃኒት አቅርቦትን ከዋናው መሥሪያ ቤት እስከ ተጠቃሚው ድረስ ያለውን ሰንሰለት ዘመናዊ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።