በደቡብ ወሎ ዞን በ10 ወራት ውስጥ ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 216 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን በ10 ወራት ውስጥ ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 216 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ
ደሴ ግንቦት 29/2015 (ኢዜአ):- በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በ2015 በጀት ዓመቱ 10 ወራት ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 216 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የዞኑ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ።
ፈቃድ ከወሰዱት ውስጥ 55ቱ ባለሀብቶች ወደ ስራ መግባታቸውን አመልክቷል።
የደቡብ ወሎ ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፋጡማ ይማም ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ ያሉትን የሰው ኃይል፣የአካባቢ ጸጋዎችና ስነ ምህዳር በመጠቀም ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በተያዘው በበጀት ዓመት 10 ወራት 23 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 216 ባለሃብቶች የኢንስትመንት ፈቃድ በመስጠት ወደ ማምረት ስራ እንዲሸጋገሩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጠው በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ግብርና፣ሪል ስቴት፣ በአገልግሎት ዘርፍ እና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች እንደሆነ ተናግረዋል።
ባለሃብቶቹ ወደ ማምረት ሲሸጋገሩ ከ43 ሺህ 700 በላይ ዜጎች አዲስ የስራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት ውስጥ 55 ባለሃብቶች በተረከቡት 251 ሄክታር መሬት ላይ ስራ በመጀመር ለሁለት ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ነው ወይዘሮ ፋጡማ ያመለከቱት።
በሌላ በኩል ባለፉት ዓመታት መሬት ወስደው ወደ ስራ ባልገቡ 25 ባለሃብቶች ላይ በተወሰደ እርምጃ 27 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን በኢንቨስትመንት ከተሰማሩ 500 ከሚጠጉ ባለሃብቶች መካከል 200 የሚሆኑት ወደ ማምረት መግባታቸውን ከዞኑ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።